የማዕድን ሚኒስቴና ተጠሪ ተቋማቱ የበጎነት ቀንን ምክንያት በማድረግ በአፋር ክልል የ1 ነጥብ 3 ሚሊዮን ብር ድጋፍ አደረጉ - ኢዜአ አማርኛ
የማዕድን ሚኒስቴና ተጠሪ ተቋማቱ የበጎነት ቀንን ምክንያት በማድረግ በአፋር ክልል የ1 ነጥብ 3 ሚሊዮን ብር ድጋፍ አደረጉ
ሰመራ ጳጉሜን 3/2015 (ኢዜአ):-የማዕድን ሚኒስቴና እና ተጠሪ ተቋማቱ የበጎነት ቀንን ምክንያት በማድረግ በአፋር ክልል ለኢረብቲ ወረዳ እና ለሰመራ ሎጊያ ከተማ ተማሪዎችና አቅመ ደካሞች የ1 ነጥብ 3 ሚሊዮን ብር የዓይነትና የገንዘብ ድጋፍ አደረጉ።
ድጋፉን ሰመራ ሎጊያ ከተማ ተገኝተው ያስረከቡት የኢትዮጵያ የማዕድን ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲቲዮት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ጉታ ለገሰ እና የኢትዮጵያ ጂኦሎጂካል ኢንስቲቲዮት ዳይሬክተር ዶክተር ደጀኔ ኀይለማሪያም ናቸው።
በድጋፉም ለኢረብቲ ወረዳ 400 ተማሪዎች እንዲሁም ለሰመራ ከተማ 100 ተማሪዎች ደብተር፣ እስክርቢቶ እና አርሳስ መበርከቱን ዶክተር ጉታ ገልጸዋል።
ከእዚህ በተጨማሪ በኢረብቲ ወረዳ ቤታቸው በጦርነት ጉዳት ለደረሰበት አምስት አባውራዎች ለቤት ማደሻ የሚሆን 300 ሺህ ብር ድጋፍ መደረጉን ጠቁመዋል።
በእዚሁ ወረዳው ለሚገኝ አንድ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት 300 ሺህ ብር ድጋፍ መደረጉንም ዶክተር ጉታ ለገሰ በድጋፍ ርክክቡ ወቅት አመልክተዋል።
የሠመራ ሎጊያ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ አብዱ ሙሳ በበኩላቸው የማዕድን ሚኒስቴር እና ተጠሪ ተቋማቱ በበጎነት ቀን ክልሉ ድረስ መጥተው ላበረከቱት ድጋፍ አመስግነዋል።
የኢረብቲ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ መሐመድ አሊዮ በወረዳው ቀደም ሲል በጦርነት ምክንያት ጉዳት መድረሱን አስታውሰው፣ የተደረገው ድጋፍ የመልሶ ሟቋቋም ሥራውን እንደሚያግዘ ተናግረዋል።
ዛሬ የገንዘብና የትምህርት ቁሳቁስ የተበረከተላቸው ወላጆች እና ተማሪዎችም ለተደረገላቸው እገዛ አመስግነዋል።