ቀጥታ፡

በጎነት መስፈርት የለውም፤ ከተረፈን ሳይሆን ካለን ማካፈልን የሚጠይቅ የመልካምነት እሴት ነው-ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ

አዲስ አበባ ፤ ጳጉሜን 3/2015 (ኢዜአ)፦ "በጎነት መስፈርት የለውም፤ ከተረፈን ሳይሆን ካለን ማካፈልን የሚጠይቅ የመልካምነት እሴት ነው" ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ተናገሩ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህን ያሉት ከተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ለመጡ በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች ባስተላለፉት መልዕክት ነው፡፡


 

ወጣቶቹ በአገር ልማት ላይ የወጣቶችን ሚና በሚመለከት ከፌደራል ከፍተኛ የመንግስት ኃላፊዎች ጋር ትናንት በአዲስ አበባ ውይይት ማድረጋቸው ይታወቃል፡፡

በዛሬው እለት ደግሞ "በጎነት ለሀገር" በሚል መሪ ሃሳብ እየተከበረ የሚገኘውን የበጎነት ቀን በወዳጅነት አደባባይ አክብረዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ በዚሁ ጊዜ እንደተናገሩት፤ በጎነት መስፈርት አልባ እና ቀስቃሽ የማያስፈልገው ተግባር ነው ብለዋል፡፡

በጎነት ከማይነጥፍ የመልካምነት ምንጭ በነጻ መስጠት መሆኑን ጠቅሰው፤ ይህም ነገን የተሻለ የሚያደርግ መልካም ዘር ነው ብለዋል፡፡

በመሆኑም ወጣቶች በበጎ ፈቃድ ማገልገልን አጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸውም ጠቅላይ ሚኒስትሩ መክረዋል፡፡

ወጣቶች አንዳንድ ሰዎች በክፋት የሚያንጸባርቁትን ሀሳብ ወደ ጎን በመተው ለኢትዮጵያ ብልጽግና በጋራ መትጋት እንዳለባቸውም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

"ኢትዮጵያ በዜጎቿ ትብብር የሚገጥሟትን ችግሮች እያሸነፈች ትቀጥላለች፤ ኢትዮጵያን በድል ከማሻገር የሚያቆመን ምድራዊ ኃይል የለም ብለዋል፡፡

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም