በጎነትን በዕለተ ተዕለት ኑሯችን ውስጥ እየተገበርነው ልንኖረው የሚገባን ጉዳይ ነው -የሰላም ሚኒስትር ብናልፍ አንዷለም - ኢዜአ አማርኛ
በጎነትን በዕለተ ተዕለት ኑሯችን ውስጥ እየተገበርነው ልንኖረው የሚገባን ጉዳይ ነው -የሰላም ሚኒስትር ብናልፍ አንዷለም

አዲስ አበባ፤ ጳጉሜን 3/2015(ኢዜአ)፦ በጎነትን በዕለተ ተዕለት ኑሯችን ውስጥ እየተገበርነው ልንኖረው የሚገባን ጉዳይ ነው ሲሉ የሰላም ሚኒስትር ብናልፍ አንዷለም ተናገሩ።
ጳጉሜን 3 የበጎነት ቀን ሲሆን 'በጎነት ለሀገር' በሚል መሪ ሃሳብ በተለያዩ መርሃ ግብሮች በአገር አቀፍ ደረጃ እየተከበረ ይገኛል።
የበጎነት ቀንን አስመልክቶ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ከሰላም ሚኒስቴርና ከሌሎች ተቋማት ጋር በመተባበር በጎነት ለሀገር በሚል ሃሳብ ከባለድርሻ አካላት ጋር የፓናል ውይይት አካሂዷል።
የሰላም ሚኒስትር ብናልፍ አንዷለም በዚሁ ጊዜ እንዳሉት እንደ አገር በሚደረገው የለውጥ ጉዞ ውስጥ በጎነት የራሱ ትልቅ ድርሻ እንዳለው ገልጸዋል።
የበጎነት ተግባርን ለመፈጸም ሰው መሆን ብቻ በቂ ነው ያሉት ሚኒስትሩ በጎነትን በዕለተ ተዕለት ኑሮአችን ውስጥ መተግባር ይገባል ሲሉም አክለዋል።
የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ በበኩላቸው በጎነት ያለ ምንም ክፍያ አገርንና ሕዝብን በማገልገል የሚገኝ ትልቅ አቅም ነው ብለዋል።
በተለይ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ወጣቶች በተደራጀ መልኩ በአገር አቀፍ ደረጃ በስፋት እየተሳተፉበት ያለው የበጎ አድራጎት ስራ ትልቅ ውጤት እያስመዘገበ መሆኑን አመልክተዋል።
በቀጣይም ይህ የበጎ አድራጎት ስራ ተጠናክሮና ባህል ሆኖ እንዲቀጥል ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በትኩረት እየሰራ መሆኑን ገልጸው፤ ይህ ተግባር በሁሉም ዜጎች ዘንድ ተጠናክሮ እንዲቀጥል አደራ ብለዋል።
የመቄዶንያ የአረጋዊያንና የአዕምሮ ህሙማን መርጃ ማዕከል መስራች ዶክተር ቢንያም በለጠ በመድረኩ ተገኝተው ባስተላለፉት መልዕክት በጎ ተግባር ሁል ጊዜም ቢሆን የህሊና ሰላም የሚሰጥ ነው ብለዋል።
በመሆኑም ይህ ተግበር መስዋዕትነት ጭምር የሚጠይቅ እና ለሌሎች የመኖር ድርሻ ነው ሲሉም አክለዋል።
የባቡልኬር በጎ አድራጎት መስራች ወይዘሮ ሀናን መሃሙድ በበኩላቸው፣ በጎ ተግባር ለሀገር ግንባታ የራሱ የሆነ ትልቅ አበርክቶ ያለውና የህሊና እረፍት የሚሰጥ ነው ብለዋል።
የዘንድሮ ዓመት የጳጉሜን ወር ቀናት የተለያዩ ስያሜዎች የተሰጣቸው ሲሆን፤ ጳጉሜን 1 የአገልጋይነት ቀን፣ ጳጉሜን 2 የመስዋዕትነት ቀን፣ ጳጉሜን 3 የበጎነት ቀን፣ ጳጉሜን 4 የአምራችነት ቀን፣ ጳጉሜን 5 የትውልድ ቀንና ጳጉሜን 6 የአብሮነት ቀን በሚል ስያሜ በተለያዩ ተግባራት ታስበው ይውላሉ።