የዕልፍ ሕጻናትን ዕጣ ፈንታ ከሞት ወደ ሕይወት የለወጠው ወጣት ላሌ ላቡኮ 

በሀገራችን በርካታ አካባቢዎች የታዳጊዎችን ተስፋና ህልም ብቻ ሳይሆን ሕልውና የሚገዳደሩ ከባህላዊ እምነት ጋር የተቆራኙ አይነተ ብዙ ጎጂ ባህላዊና ልማዳዊ ድርጊቶች እና ክዋኔዎች አሉ።

ለአብነትም ደቡብ ኦሞ ዞን እንደ ካራ፣ ሀመርና ቤና ህዝቦች ዘንድ የተለመደው እና ከህጻናት ጥርስ አበቃቅል ጋር የተያያዘው ’ሚንጊ' የሚሰኘው ጎጂ ልማዳዊ ድርጊት ይጠቀሳል።

በአካባቢው ልማድ በታችኛው ድድ ጥርስ የሚያበቅሉ እንስሳት ቅዱስ፣  በላይኛው ድድ ጥርስ የሚያበቅሉ እንስሳት ደግሞ ርኩስ የሚል ስያሜ ይሰጣቸዋል።

ከዚህ ጋር በማገናኘትም የሚወለዱ ህጻናት የላይኛው የወተት ጥርሳቸው ቀድሞ የሚበቅል ከሆነ እንደ እርኩሳን እንስሳት ከመጥፎ መንፈስ ጋር ተቆጥሮ ለማህበረሰቡ የማይበጅ፣ አድጎም ለቤተሰቡ ጠንቅ ተቆጥሮ የመገደል ዕጣ ፈንታ ይገጥመዋል።

ይህ ልማድ “ሚንጊ” ተብሎ የሚጠራ ሲሆን አያሌ ህጻናትን ቀጥፏል።

ይህ ብቻም ሳይሆን የማህበረሰቡ አባል ሴት ከትዳር በፊት ልጅ ከወለደች የተወለደው ሕጻን  በ'ሚንጊ'ነት ይፈረጃል።

ሚንጊ ተብለው የተፈረጁ ህጻናት በማህበረሰቡ ዘንድ መርገምት፣ ቁጣ፣ ርሀብ በሽታ… እንደሚያመጡ ስለሚቆጠር ከጥልቅ ወንዝ መጣል፣ ወደ ገደል መወርወር አልያም በጫካ ውስጥ የመጣል ዕጣ ይገጥማቸዋል።

ሚንጊንና መሰል በየማህበረሰቡ ዘንድ ለዘመናት የተለመዱ ጎጂ ድርጊቶችን ለማስቀረት እና ማህበረሰብ አቀፍ ለውጥ ለማምጣት ግን ውስብስብ እና ጊዜ የሚጠይቅ ጉዳይ ነው።

ላሌ ላቡኮና መሰል ብርቱና አርቆ አሳቢ ሰዎች ግን ባደጉበት ብርቱ ጥረት የማህብረሰብን አስተሳስብ በመለወጥ ለዘመናት ለሚከወኑ ውስብስብ ችግሮችን መፍትኤ መስጠት ችለዋል።

ላሌ ላቡኮ በተወለደበት ቀዬ እና አባል በሆነበት ደመ ከልብ ሆነው የሚቀሩ ህጻናትን ዕጣ ፈንታ ከወንዝ፣ ከገደልና ከጫካ ከመጣል ተርፈው ለወግና ማዕረግ እንዲበቁ አስችላል።

በአጉል ባህል ሕይወታቸውን የሚነጠቁ ዕልፍ አዕላፍ ህጻናት ነፍስ እንዲዘሩ በማድረግ ትውልድ ያሻገረ፣ ማህበረሰብን የለወጠ አርበኛ ነው።

ላሌ ላቡኮ ይህን ነባር ጎጂ ልማዳዊ ድርጊት ለመቃወምና መፍትሄ ለማምጣት ያነሳሳው ሁለት እህቶቹን ጨምሮ ምንም ነፍስ ያላወቁ ሕጻናት በሚንጊነት ተፈርጀው ሲቀጠፉ  በማየቱና በመስማቱ እንደሆነ ይናገራል።

ከ17 ዓመታት በፊት ‘ኦሞ ቻይልድ’ በሚል ባቋቋመው ድርጅት 'ሚንጊ' የተባሉ 58 ሕፃናትን ከገዳዮች ፈልቅቆ ከሕልፈት ወደ ሕይወት ለውጧል፣ ለቁም ነገር ለማብቃትም እያስተማራቸው ይገኛል።


 

እህቶቹን ጨምሮ የትውልድ መንደሩ ሕጻናትን ሕይወት ለመቀጠፍ የዳረጋቸው የሚንጊ ድርጊት የሚፈጸመው፣ በማህበረሰቡ ዕውቀት ማነስ ነው ብሎ ያምናል።

በዚህም ይህን አስከፊ ድርጊት እና አስተሳሰብ ለመቀየር ቆርጦ በመነሳቱ ቤተሰቡን ጨምሮ ከማህበረሰቡ መገለል እስከ ማስፈራሪያ ጥቃቶች አስተናግዷል።

እርሱ ግን ፈተናዎች ሳይበግሩት በዓላማው ጸንቶ፣ ትዕግስትና ብልሃት ተላብሶ ሸውራራ ማህበረሰብ አቀፍ አመለካከቶችን መስበር ችሏል።

የሚንጊ ባህል አሁንም ሙሉ ለሙሉ እንዳልተቀረፈ የሚናገረው ላሌ፣ ስር ነቀል የአስተሳስብ ለውጥ ለማምጣት ለህብረተሰቡ አሁንም ብርቱ ግንዛቤ የመፍጠር ስራዎች እንደሚገቡ ገልጿል።

ላሌ በመሰረተው ድርጅት ከሚማሩ ሕጻናት ባሻገር ከ300 በላይ ህጻናት ከቤተሰባቸው ዘንድ ሆነው ለመማር እንዲችለኩ ማድረጉንም ይናገራል።

ሕፃናቱን ከሞት አፋፍ ታድጎ ከራሳቸው ሕልውና ባለፈ ለቁም ነገር እንዲበቁና ለሀገርና ለወገን የሚበጁ ሰዎች እንዲሆኑ በመስራቱ አዕምራዊ እርካታ እንደሚሰማው ይገልጻል።

ላሌ የሚንጊን ጎጂ ድርጊት ከመታደጉ በተጨማሪ በደቡብ ኦሞ  ትምህርት ቤት ገንብቶ ከ700 በላይ ተማሪዎችን እያስተማረ ይገኛል።

ናሽናል ጂኦግራፊ፣ ቴድ ቶክ፣ የሰብዓዊ መብቶች ተቋም እና የበጎ ሰው ሽልማት ድርጅት የላሌን ትውልድ የመታደግ ተግባር ዕውቅና ከሰጡት ወስጥ ይጠቀሳሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም