ኢትዮጵያ በአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ዛሬ ከግብጽ ጋር ትጫወታለች

አዲስ አበባ፤ ጳጉሜን 3/2015(ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በኮትዲቭዋር አስተናጋጅነት ለሚካሄደው 34ኛው የአፍሪካ ዋንጫ የምድብ የመጨረሻ የማጣሪያ ጨዋታውን ዛሬ ከግብጽ ጋር ያደርጋል።   

የሁለቱ ብሔራዊ ቡድኖች ጨዋታ በካይሮ 'June 30 Stadium' ከምሽቱ 1 ሰዓት ላይ ይከናወናል።

በጊዜያዊ ዋና አሰልጣኝ ኢንስትራክተር ዳንኤል ገብረማርያም የሚመራው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ለጨዋታው ከነሐሴ 23 እስከ 28/2015 በአዲስ አበባ ዝግጅቱን ሲያደርግ ቆይቷል።

ቡድኑ ለዛሬው ጨዋታ የመጨረሻ ልምምዱን ጨዋታውን በሚያደርግበት 'June 30 Stadium' አከናውኗል።

ሁሉም የስብስቡ አባላትም በተሟላ ጤንነት ልምምዳቸውን እንዳደረጉ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አስታውቋል።


 

ኢንስትራክተር ዳንኤል ገብረማርያም ከጨዋታው በፊት በሰጡት መግለጫ ኢትዮጵያ በማጣሪያው ከምድቧ  ብትወድቅም ቡድናቸው ጨዋታውን ለቀጣይ የዓለም ዋንጫና የአፍሪካ አገራት እግር ኳስ ሻምፒዮና (ቻን) የማጣሪያ ውድድሮች መዘጋጃ እንደሚጠቀምበት ገልጸዋል።

በመጀመሪያ የማጣሪያ ጨዋታ ኢትዮጵያ ግብጽን 2 ለ 0 ማሸነፏን አውስተው፤ በዛሬው ጨዋታም መልካም ውጤት ለማምጣት ዝግጅት መደረጉን ተናግረዋል።

በ53 ዓመቱ ፓርቹጋላዊ አሰልጣኝ ሩዊ ቪቶሪያ የሚመራው የግብጽ ብሔራዊ ቡድን በማጣሪያው በምድብ አራት 12 ነጥብ በመያዝ ለአፍሪካ ዋንጫ ማለፉ ይታወቃል።

የ30 ዓመቱ ጋቦናዊ ፓትሪስ ታንጉይ ሜቢያሜ የሁለቱን ብሔራዊ ቡድኖች በዋና ዳኝነት ይመሩታል።

በአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ በምድብ አራት የሚገኘው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በአራት ነጥብ የመጨረሻውን ደረጃ የያዘ ሲሆን ከምድቡ አስቀድሞ መውደቁ የሚታወስ ነው።

በዚሁ ምድብ ጊኒ ግብጽን ተከትላ ለአፍሪካ ዋንጫ ማለፏ ይታወቃል።


 

ሁለቱ ብሔራዊ ቡድኖች በሐምሌ ወር 2014 በማላዊ ቢንጉ ብሔራዊ ስታዲየም ባደረጉት የማጣሪያ ጨዋታ ኢትዮጵያ በሽመልስ በቀለና ዳዋ ሆቴሳ ግቦች ግብጽን 2 ለ 0 ማሸነፏ የሚታወስ ነው።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም