የፌደራል ፖሊስ አባላት በመስዋዕትነታቸው የኢትዮጵያን ሰላምና አንድነት አፅንተው ያስቀጥላሉ-ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገብረሚካኤል - ኢዜአ አማርኛ
የፌደራል ፖሊስ አባላት በመስዋዕትነታቸው የኢትዮጵያን ሰላምና አንድነት አፅንተው ያስቀጥላሉ-ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገብረሚካኤል
አዲስ አበባ ፤ ጳጉሜን 2/2015 (ኢዜአ) ፡- የፌደራል ፖሊስ አባላት መስዋዕትነት በመክፈል የሀገርን ሰላምና አንድነት የማፅናት ሃላፊነታቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገብረሚካኤል ገለጹ።
የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ የጀግኖች ማዕከልን ዛሬ አስመርቋል፡፡
የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገብረ ሚካኤል በምርቃት ስነ-ስርዓቱ ላይ እንዳሉት የፌደራል ፖሊስ የኢትዮጵያን ሰላምና የህዝቦቿን ደህንነት ለማስጠበቅ ከፍተኛ መስዋዕትነት እየከፈለ ነው፡፡
የፌደራል ፖሊስ አባላት የሀገርን አንድነት ለማጽናት በሚያደርጉት ጥረት ውስጥ የተለያዩ ጉዳቶችና አደጋዎች እንደሚያጋጥማቸው አንስተዋል፡፡
ለአገራቸው ክብር ሲታገሉ ጉዳት የሚያጋጥማቸው የፖሊስ አባላት ከዚህ ቀደም በአግባቡ የሚረዱበት ማቆያ ባለመኖሩ በማይመቹ ቦታዎች ላይ ድጋፍና እንክብካቤ ሲደረግላቸው እንደነበረ ተናግረዋል፡፡
ችግሩን ለመፍታት ባለፉት ዓመታት የተለያዩ ጥረቶች መደረጋቸውን በማንሳት፤ ዛሬ የተመረቀው የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ የጀግኖች ማዕከል አንዱ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ቀደምት ኢትዮጵያውያን ለሀገራችን ክብርና ልዕልና ከፍተኛ መስዋዕትነት መክፈላቸውን ያነሱት ኮሚሽነር ጀነራሉ፤ የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስም የሀገርን አንድነት ለማፅናት የትኛውንም ዋጋ ለመክፈል ዝግጁ መሆኑን አረጋግጠዋል።
በተለይም በአሁኑ ወቅት የውጭና የውስጥ ጠላቶች በሀገራችን ላይ ችግር ለመፍጠር እየሞከሩ መሆኑን በመጥቀስ፤ የፌደራል ፖሊስ አባላት የጠላትን እቅድ በማክሸፍ የሀገርን ሰላም ያስጠብቃሉ ነው ያሉት።
ህብረተስቡም ለፀጥታ አካላት የሚያደርገውን ትብብር አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል።
በማዕከሉ ህክምና ከተደረገላቸው የፖሊስ አባላት መካከል ዋና ሳጅን ኢብሳ ለማና ምክትል ኢንስፔክተር ገበየሁ አወቀ ማዕከሉ በመገንባቱ መደሰታቸውን ተናግረዋል።
ማዕከሉ ከዚህ ቀደም የነበሩ ችግሮችን በመፍታት የተሻለ የህክምና እርዳታና ድጋፍ ለመስጠት እንደሚያስችልም ነው የገለጹት።
በማዕከሉ ምርቃት ስነ-ስርዓት ላይ የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ከፍተኛ አመራሮች፣ የፖሊስ አባላትና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።