ለኢትዮጵያ አንድነትና ሉዓላዊነት መከበር ለከፈልነው መስዋዕትነት ሁሌም ክብርና ኩራት ይሰማናል - የቀድሞ ጦር ሰራዊት ከፍተኛ መኮንኖች - ኢዜአ አማርኛ
ለኢትዮጵያ አንድነትና ሉዓላዊነት መከበር ለከፈልነው መስዋዕትነት ሁሌም ክብርና ኩራት ይሰማናል - የቀድሞ ጦር ሰራዊት ከፍተኛ መኮንኖች
አዲስ አበባ፤ ጳጉሜን 2/2015(ኢዜአ)፦ ለኢትዮጵያ አንድነትና ሉዓላዊነት መከበር ለከፈልነው መስዋዕትነት ሁሌም ክብርና ኩራት ይሰማናል ሲሉ የቀድሞ የጦር ሰራዊት ከፍተኛ መኮንኖች ተናገሩ።
የኢትዮጵያን ክብርና ሉዓላዊነት በጀግንነት ጠብቆ በማዝለቅ የቀድሞ ሰራዊትና አጠቃላይ ህዝቡ ያበረከተው አስተዋጽኦ በዘመናት የማይጠፋ ታሪክ ነው።
በተለይም በግዳጅ ቀጠናዎች በጀግንነትና በወኔ ለኢትዮጵያ ክብር መስዋእትነት የከፈሉ በርካታ ጀግና የቀድሞ ሰራዊት አመራሮችና አባላት ይጠቀሳሉ።
ከእነዚህ መካከል ከ30 ዓመታት በላይ ኢትዮጵያን ያገለገሉት የቀድሞ ሰራዊት ከፍተኛ መኮንን ብርጋዴር ጀኔራል ዋሲሁን ንጋቱ፤ ኢትዮጵያን አጽንቶ ለማቆየት በርካቶች በጀግንነት መስዋእትነት ስለመክፈላቸው ይናገራሉ።
ከ1956 እስከ 1969 ዓ.ም በምስራቅ ኢትዮጵያ የነበረውን የውጭ ወረራ ጨምሮ በተለያዩ አጋጣሚዎች የተቃጡ ወረራዎችን በመመከት በርካታ ጀግኖች መስዋእትነት መክፈላቸውን አስታውሰዋል።
በመሆኑም ለሀገር ሰላም፣ አንድነት፣ ሉዓላዊነትና ክብር ለተከፈለው ዋጋ ሁላችንም ክብርና ኩራት ይሰማናል ብለዋል።
በቀድሞው የሆለታ ገነት ጦር ትምህርት ቤት የ17ኛ ኮርስ ምሩቅ እና ሀገራቸውን 34 ዓመታት በወታደራዊ መኮንንነት ያገለገሉት ብርጋዴር ጀኔራል ካሳ ወልደሰማያት፤ ለሀገር የሚከፈል ዋጋ በየትኛውም መመዘኛ ክብርና ኩራት መሆኑን ገልጸዋል።
ለሀገራቸው ዘብ ከመሆን ባለፈ በኮንጎ ሰላም አስከባሪ ጦር ኢትዮጵያን በመወከል በክብር ዘበኛ የጠቅል ሻለቃ ጦር ዘማቾች አንዱ የሆኑት ብርጋዴር ጀኔራሉ ያበረከቱት ሁሉ ለአገር የተከፈለ ዋጋ በመሆኑ ኩራት ይሰማኛል ብለዋል።
ከአፄ ሃይለስላሴ ዘመነ መንግስት በቀድም ሰራዊት አባልነት ሀገራቸውን ያገለገሉት ሸለቃ ድሪባ ገመቹ፤ የሀገር ሕልውና ያለመስዋዕትነት እንደማይመጣ ይናገራሉ።
በተለያዩ ዐውደ ግንባሮች ለኢትዮጵያ አንድነትና ሉዓላዊነት መውደቃቸውን አስታውሰው፤ በዚህም ትልቅ ክብርና ኩራት ይሰማኛል ብለዋል።
ጳጉሜን 2 ቀን የመስዋእትነት ቀን ሆኖ "በመስዋእትነት የምትጸና ሀገር " በሚል መሪ ሃሳብ በሀገር አቀፍ ደረጃ በተለያዩ መርሃ ግብሮች ተከብሯል።