ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ያስገነባውን የጀግኖች ማዕከል አስመረቀ

አዲስ አበባ ፤ ጳጉሜን 2/2015 (ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ በግዳጅ ላይ ጉዳት ለደረሰባቸው የፖሊስ አመራርና አባላት ያስገነባውን የጀግኖች ማዕከል አስመረቀ።

የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገብረሚካኤል፣ ጀግኖቻችን ኢትዮጵያን ለማፅናት በጀግንነት ሲፋለሙ አደጋ ሲያጋጥማቸው የፖሊስ ማስተናበሪያ በጣም አነስተኛ አገልግሎት የሚሰጥና ምቹ እንዳልነበር ተናግረዋል፡፡

በኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ኮርፖሬሽን ሙሉ ወጪ በአንድ ዓመት ከስምንት ወር ግንባታውን አጠናቆ በዛሬው ዕለት ለምረቃ እንዲበቃ በማድረጉ ኮሚሽነር ጀነራሉ አመስግነዋል።

አባቶቻችን ለሀገራችን በጀግንነት መስዋዕትነት ከፍለው በኩራት እንዳስረከቡን ሁሉ እኛም የሀገራችንን የውስጥና የውጭ ጠላቶች በመመከት በመስዋዕትነት ጠብቀን ለትውልድ እናስረክባለን ብለዋል፡፡

የፖሊስ ሠራዊቱ ከኢትዮጵያ ሕዝብ አብራክ የወጣ በመሆኑ በሚንቀሳቀስበት ቦታ ሁሉ አስፈላጊውን ድጋፍና እገዛ ሲያደርግ እንደነበረ ሁሉ በቀጣይም ድጋፉን አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ አስተዳደርና ልማት ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ምክትል ኮሚሽነር ጀነራል ነብዩ ዳኜ ኢትዮጵያን ማገልገል ዓላማው አድርጎ ከቤቱ የወጣ ወጣት ጉዳት ሲያጋጥመውና ለሀገሩ ሲል ጉዳት ያስተናገዱ ጀግኖቻችን ዳግም ህይወታቸውን እየመሩ ሀገራቸውን እንዲያገለግሉ የሚያደርግ የጀግኖች ማዕከል በመገንባቱ እንኳን ደስ አላችሁ ብለዋል።

የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ስራዎች ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈጻሚ ኢንጅነር ዮናስ አያሌው በበኩላቸው ማዕከሉ ከ200 ሚሊየን ብር በላይ ወጭ ተደርጎበት የተገነባ መሆኑን ተናግረዋል።

ማዕከሉ በግዳጅ ላይ ጉዳት የደረሰባቸው የፖሊስ ሠራዊት የህክምና አገልግሎት የሚያገኙባቸው ክሊኒኮች፣ የእንጨትና የብረታ ብረት ስራዎችን የሚሰሩበት ዎርክሾፕ፣ ጅምናዝየም እንዲሁም ካፍቴሪያዎችን ያካተተ መሆነ ጠቅሰው ለኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ የሚያደርጉትን ድጋፍ አጠናክረው እንደሚቀጥሉ አስታውቀዋል።

በምረቃ ስነ-ስርዓቱ ላይም የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ስራዎች ኮርፖሬሽን ማኔጅመንት አባላት፣ የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ምክትል ኮሚሽነር ጀነራሎችና ከፍተኛ አመራሮች፣ ጀግኖች የፖሊስ አባላት እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች መገኘታቸውን የፌዴራል ፖሊስ መረጃ ያመለክታል።

 

 

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም