ቀጥታ፡

ጀግኖች በመስዋዕትነት ያቆዩዋትን ኢትዮጵያን ትውልዱ አጽንቶ ሊያስቀጥላት ይገባል-ጀግኖች አርበኞች

ጎንደር ፤ ጳጉሜን 2/2015 (ኢዜአ)፡-ቀደምት ጀግኖች አባቶች የህይወት መስዋዕትነት ከፍለው ያቆዩዋትን ኢትዮጵያ ትውልዱ አጽንቶ ሊያስቀጥላት እንደሚገባ የሰሜን ጎንደር ዞን ጀግኖች አርበኞች ማህበር አባላት ተናገሩ፡፡

የዛሬው የመስዋዕትነት ቀንን አስመልክቶ የማህበሩ አባላት ለኢዜአ በሰጡት አስተያየት፤ ኢትዮጵያ ዳር ድንበሯ ተከብሮ የቆየው ጀግኖች አርበኞች እምቢ ለሀገሬ እምቢ ለወገኔ ብለው በከፈሉት መስዋዕትነት መሆኑን አመልክተዋል፡፡

የማህበሩ ሊቀ-መንበር አቶ ይርጋ በላይ እንዳሉት፤ ለሀገር መስዋዕት መሆን የጥንት አባቶቻችን ያቆዩት እሴት ከመሆኑም በላይ የነጻነትና የአርበኝነት የተጋድሎ ልዩ ምልክት ነው፡፡

ኢትዮጵያ ታፍራና ተከብራ የኖረችው በጀግኖች ልጆቿ መስዋዕትነት እንደሆነ ጠቅሰው፤ አሁንም ሀገር ጸንታ እንድትቀጥል ትውልዱ የአባቶቹን አኩሪ የተጋድሎ ታሪክ ሊያስቀጥል ይገባል ብለዋል፡፡

የሀገር አለኝታና መከታ የሆነው የሀገር መከላከያ ሰራዊት ትውልዱ ትልቅ አክብሮት ሊሰጠው እንደሚገባ ያሳሰቡት የማህበሩ አባል አባት አርበኛ መስፍን አያሌው ናቸው፡፡

መከላከያ ሰራዊት ከህዝብ አብራክ የወጣ ለሀገር ዳር ድንበር መከበር ዘብ የቆመ፣ በተለያዩ ጊዜያትም ለኢትዮጵያ አንድነትና ለህዝቡ ሰላም ሲል መስዋዕትነት የከፈለ ውድ የኢትዮጵያ ልጅ ነው ብለዋል፡፡

ትውልዱ የቀደምት አባቶቹን የተጋድሎ ታሪክና እሴቶች አውቆና ጠብቆ ማስቀጠል እንዲችል እኛ ጀግኖች አርበኞች በማስተማርና በማስገንዘብ የድርሻችን ለመወጣት ዝግጁ ነን ሲሉ አስታውቀዋል፡፡

ሌላው አባት አርበኞች ማህበር አባል አቶ ዘመነ አያሌው በበኩላቸው፤ በተለያዩ ጊዚያት ኢትዮጵያን በመውረር ጦር የሰበቁ የውጪ ወራሪዎች ተቀጥተው የተመለሱት ቀደምት ጀግኖች አርበኞች በከፈሉት መስዋዕትነት መሆኑን አስታውሰዋል፡፡

አሁንም የሃገርን ዳር ድንበር በማስከበር የተከበረች ኢትዮጰያን ለመጪው ትውልድ ለማስተላለፍ ወጣቱ ትውልድ ያለውን ሃገራዊ ፍቅርና አክብሮት ማጠናከር እንዳለበት ተናግረዋል።

"በመስዋዕትነት የምትጸና ሀገር" በሚል መሪ ሀሳብ የመስዋትነት ቀን በተለያዩ ዝግጅቶች ዛሬ በኢትዮጵያ ደረጃ እየተከበረ ይገኛል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም