ሀገርን ወደ ብልጽግና ለማሻገር ለሚከናወኑ ሥራዎች ስኬታማነት ወጣቶች የበኩላቸውን መወጣት አለባቸው--ከንቲባ ከድር ጁሃር - ኢዜአ አማርኛ
ሀገርን ወደ ብልጽግና ለማሻገር ለሚከናወኑ ሥራዎች ስኬታማነት ወጣቶች የበኩላቸውን መወጣት አለባቸው--ከንቲባ ከድር ጁሃር
ድሬዳዋ፤ ጳጉሜን 2/2015 (ኢዜአ)፡-በጀግኖች መስዋዕትነት ጸንታ የቆየችውን ሀገር ወደ ብልጽግና ለማሻገር የሚሰሩ ሥራዎች ስኬታማ እንዲሆኑ ወጣቶች የበኩላቸውን መወጣት እንዳለባቸው የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ ከድር ጁሃር ተናገሩ።
ጳግሜን 2 የመስዋዕትነት ቀን "በመስዋዕትነት የምትፀና አገር" በሚል መሪ ሃሳብ በወታደራዊ ሰልፍ እና ትዕይንት ዛሬ በድሬዳዋ ተከብሯል።
በበዓሉ ላይ የተሳተፉት የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ ከድር ጁሃር እንደተናገሩት፤ ኢትዮጵያ በጀግኖች አባቶች መስዋዕትነትና በህዝቦች ደጀንነት ነጻነቷና ሉአላዊነቷ ተከብሮ የኖረች አገር ናት።
በትውልድ ቅብብሎሽና መስዋዕትነት የፀናች አገርን ለማቆየትና ለህዝብ ደህንነት መስዋዕት እየከፈሉ ላሉ የጸጥታ አካላት ክብርና ሞገስ ለመስጠት ቀኑን መከበሩን ገልፀዋል።
የተጀመረውን ሀገራዊ ለውጥ ወደላቀ ደረጃ ለማድረስ ሁሉም በተሰማራበት የሥራ መስክ ሌብነትና ብልሹ አሠራርን ከመጠየፍ ባለፈ ተግቶ ሊሰራ እንደሚገባም ከንቲባ ከድር ተናግረዋል።
በተለይ ወጣቶች የአገርን ክብርና ሉአላዊነት ጠብቆ በማቆየት የብልፅግና ጉዞን ለማሳካት የሚከናወኑ ስራዎች ስኬታማ እንዲሆኑ ተግተው መስራት እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።
"በአዲሱ አመት አንድ በሚያደርጉ ጉዳዮች ላይ በማተኮር በክልሉ የሰፈነውን ሰላምና ልማት አጠናክሮ ለማስቀጠል መስራት እንደሚገባም ተናግረዋል።
"የአገርን ሉአላዊነት በማስከበር ሂደት ሁሉም የራሱ አስተዋጽኦ ቢኖረውም የፀጥታ ኃይሉ በላቀ ጀግንነት ህይወቱን ጭምር እየከፈለ አገርን ለትውልድ ሲያስተላልፍ የነበረ፣ ያለና የሚኖሩ ነው" ያሉት ደግሞ የድሬዳዋ አስተዳደር የፍትህ ፀጥታና የህግ ጉዳየች ቢሮ ኃላፊ አቶ አብዱልሰላም አህመድ ናቸው።
መስዕዋትነት እየከፈለ ላለው የአገር የመከላከያ ሠራዊት፣ የፖሊስና የሚሊሻ አካላት እንዲሁም ለሌሎች የፀጥታ ሃይሎች ክብርና ሞገስ ለመስጠት ቀኑ መከበሩ መልካም አጋጣሚ መሆኑንም ተናግረዋል።
ህብረተሰቡም ሰላሙን ለማደፍረስ የሚንቀሳቀሱ አካላትን ከጸጥታ አካላት ጎን በመሆን በመከላከል የተጀመረውን የለውጥ ጉዞ ዳር ማድረስ እንዳለበት አስገንዝበዋል።
የመስዋዕትነት ቀኑን የአገር የመከላከያ ሠራዊት፣ የፌደራልና የድሬዳዋ ፖሊስና ሚሊሻ እንዲሁም የኢፌድሪ አየር ኃይል የድሬዳዋ አየር ምድብ የሠራዊት አባላት በታላቅ ሰልፍ እና ትዕይንት አክብረዋል።
በስነስርዓቱ ላይ የተሳተፉት የኢፌድሪ አየር ኃይል የድሬዳዋ ምድብ አባል ሻንበል ሸጋው አገኘሁ ለኢዜአ እንዳሉት፤ "ቀኑ በድምቀት መከበሩ ከሚያላብሰው ክብር ባለፈ ለአገር ሉአላዊነት የተጀመረውን ቅንጅታዊ ሥራ ያጠናክራል" ብለዋል።
የፌደራል ፖሊስ አባል ረዳት ኢንስፔክተር ዘካሪያስ ፋንታሁን በበኩላቸው፤ "በመላው አገሪቱ የተከበረው የመስዋዕትነት ቀን በሠራዊቱና በዜጎች መካከል መቀራረብና ህብረ ብሔራዊ አንድነት ይፈጥራል" ብለዋል።
የአገሪቱን ዳር ድንበር የማስከበርና የዜጎችን ደህንነት የማረጋገጥ ተልኳቸውን ይበልጥ ለመወጣት ከምንግዜውም ባላይ ዝግጁ መሆናቸውንም አረጋግጠዋል።
ዛሬ በድሬደዋ በተከበረው የመስዋዕትነት ቀን ላይ የድሬዳዋ አስተዳደር ምክር ቤት አፈ ጉባኤ እና የካቢኔ አባላት፤ የድሬዳዋ የኃይማኖት አባቶች፣ የአገር ሽማግሌዎች፣ ዑጋዞች፣ አባገዳዎች እና ነዋሪዎች ተሳትፈዋል።