ኢትዮጵያ በ78ኛው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ ውጤታማ የዲፕሎማሲ ስራ ለማከናወን ዝግጅት አድርጋለች-የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ በ78ኛው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ ውጤታማ የዲፕሎማሲ ስራ ለማከናወን ዝግጅት አድርጋለች-የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር
አዲስ አበባ ፤ ጳጉሜን 2/2015 (ኢዜአ) ፡- ኢትዮጵያ በመጪው መስከረም ወር ለሚካሄደው 78ኛው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ ውጤታማ የዲፕሎማሲ ስራ ለማከናወን ዝግጅት ማደረጓን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል።
ሚኒስቴሩ ኢትዮጵያ በአዲሱ ዓመት በሁለትዮሽና በባለብዙ ወገን ዲፕሎማሲ አጋሮችን የማብዛት ስራዋን አጠናክራ እንደምትቀጥልም ገልጿል።
የሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ አምባሳደር መለስ ዓለም ዛሬ ለመገናኛ ብዙሃን ሳምንታዊ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል።
አምባሳደር መለስ በመግለጫቸው በመጀመሪያው የኢትዮ-ሶማሊያ የሚኒስትሮች የጋራ ኮሚሽን ስብሰባና በመስከረም ወር 2016 ስለሚካሄደው 78ኛው የተባበሩት መንግስታት ጠቅላላ ጉባኤ አስመልክተው መረጃ ሰጥተዋል።
የጋራ ኮሚሽን ስብሰባውን በተመለከተ ባለፉት ሁለት ቀናት በባለሙያ ደረጃ ውይይቶች ሲካሄዱ መቆየታቸውን ገልጸዋል።
በሚኒስትሮች ስብሰባው ላይ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን እየተሳተፉ እንደሚገኙ ተናግረዋል።
በስብሰባው ሁለቱ አገራት ከዚህ ቀደም ያደረጓቸው ስምምነቶች ያሉበት ሁኔታ እየተገመገመ እንደሚገኝና የጸጥታና ደህንነት እንዲሁም ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ምክክር እየተደረገባቸው እንደሚገኝ አመልክተዋል።
ስብሰባው የኢትዮጵያና የሶማሊያ ግንኙነት በሁሉም መስኮች እንዲጠናከርና ትብብሩ ወደ ተሻለ ምዕራፍ እንዲያድግ አስተዋጽኦ ያደርጋል ነው ያሉት ቃል አቀባዩ።
78ኛው የተባበሩት መንግስታት ጠቅላላ ጉባኤ በተመለከተም ኢትዮጵያ የነቃ ተሳትፎ ለማድረግ ዝግጅት ማድረጓን አምባሳደር መለስ ገልጸዋል።
ጉባኤው በ174 አጀንዳዎች ላይ ይመክራል ተብሎ ይጠበቃል ያሉት አምባሳደር መለስ፤ ወደ ስፍራው የሚያቀናው የኢትዮጵያ ልዑክ በ55 አጀንዳዎች ላይ ንግግር በማድረግ የኢትዮጵያን አቋም ይፋ ያደርጋልም ብለዋል።
ኢትዮጵያ መድረኩን በመጠቀም አጋሮቿን በማብዛት ብሔራዊ ጥቅሞች እንዲረጋገጡና አህጉራዊ አጀንዳዎች እንዲሳኩ ለማድረግ በቂ ዝግጅት ማድረጓን ነው ቃል አቀባዩ የተናገሩት።
ኢትዮጵያ ከጉባኤው ጎን ለጎን ከአገራት ጋር ያላትን የሁለትዮሽ ትብብር ለማጠናከር እንደምትሰራም አብራርተዋል።
ኢትዮጵያ በአዲሱ ዓመት በሁለትዮሽና በባለብዙ ወገን ዲፕሎማሲ አጋሮችን የማብዛት ስራዋ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ነው ያረጋገጡት።