ቀጥታ፡

የመጀመሪያው የኢትዮ-ሶማሊያ የጋራ የሚኒስትሮች ኮሚሽን ጉባኤ በሞቃዲሾ ተካሄደ

አዲስ አበባ ፤ ጳጉሜን 2/2015 (ኢዜአ)፦ የመጀመሪያው የኢትዮ-ሶማሊያ የጋራ የሚኒስትሮች ኮሚሽን ጉባኤ በሶማሊያ ሞቃዲሾ ከተማ ዛሬ ተካሂዷል።

የሚኒስትሮች የጋራ ጉባኤው ትናንት እና ከትናንት በስቲያ ሲካሄድ የቆየው የሁለቱ ሀገራት የከፍተኛ የስራ ሀላፊዎች መድረክ የቀጠለ መሆኑ ተመላክቷል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን እንዲሁም የሶማሊያ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ሳላህ አህመድ ጃማ ጉባኤውን መርተውታል።

አቶ ደመቀ መኮንን በጉባኤው መክፈቻ ላይ ባደረጉት ንግግር በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን ግንኙነት ለማጠናከር የትብብር መስኮችን ማስፋት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ በባህልና በቋንቋ እንዲሁም የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት በርካታ ጉዳዮች እንደሚጋሩ ጠቅሰው፤ በተለይ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቱን ማጠናከር የሀገራቱን ታሪካዊ ግንኙነት ለማጎልበት ከፍተኛ ሚና እንዳለው አስገንዝበዋል።

አቶ ደመቀ በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን ዘርፈ ብዙ ግንኙነት ለማጠናከር የኢትዮጵያ መንግስት ፍላጎት እንዳለውና ለዚህም እንደሚሰራ ጠቁመዋል።

በተጨማሪም የፕሬዝዳንት ሀሰን ሼክ ሙሃመድ መንግስት አልሻባብን ለማጥፋት እያደረገ ያለውን ጥረት ያደነቁት አቶ ደመቀ ፤ ይህም በሶማሊያ ቀጣይነት ያለው ሰላምና ደህንነት ለማረጋገጥ ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል።

የሶማሊያ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ሳላህ አህመድ ጃማ በበኩላቸው በኢትዮጵያ እና በሶማሊያ መካከል ያለው ታሪካዊ ግንኙነት የሁለቱን ሀገራት ህዝቦች ጥቅም በማስከበር ላይ የተመሰረተ መሆኑን አስገንዝበዋል።

የጋራ የሚኒስትሮች ኮሚሽን ጉባኤም በሀገራቱ መካከል ያለውን ታሪካዊ ግንኙነት ለማጠናከር የጎላ ሚና እንዳለው ገልጸዋል።

በጉባኤው ላይ የንግድ ትብብር የመግባቢያ ሰነድ በሁለቱ ሀገራት ባለስጣናት በኩል መፈረሙንም ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመላክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም