ቀጥታ፡

የነፍስ አድን ስራ የበርካቶችን ህይወት ማዳን በመሆኑ ትልቅ ክብርና ኩራት ይሰማናል -  የእሳትና ድንገተኛ አደጋ ባለሙያዎች

አዲስ አበባ ፤ ጳጉሜ 2/ 2015 (ኢዜአ):-በነፍስ አድን ስራ  የበርካቶችን ህይወት ማዳን በመሆኑ ትልቅ ክብርና ኩራት ይሰማናል ሲሉ የእሳትና ድንገተኛ አደጋ ባለሙያዎች ገለጹ፡፡

የእሳትና ድንገተኛ አደጋ ባለሙያዎች አደጋን በመጋፈጥ የሰዎችን ህይወትና ንብረት ለማዳን  በሚያደርጉት ትንቅንቅ ጉዳት የሚገጥማቸውና ህይወታቸውን ጭምር የሚያጡ አሉ።

የትኛውንም አደጋ ፊት ለፊት በመጋፈጥ በተለይም የህፃናትን፣ አረጋዊያንንና ሌሎችንም ህይወት መታደግ መቻል ድፍረትና ጀግንነትን የሚጠይቅ መሆኑን የዘርፉ ባለሙያዎች ይናገራሉ።


 

ከ10 ዓመታት በላይ እሳትን በማጥፋትና ለድንገተኛ አደጋዎች ፈጣን ምላሽ በመስጠት በርካታ ተግባራትን ያከናወነው ፍቃዱ ከበደ አሁንም በሙያው እያገለገለና የዘርፍ ሃላፊም ሆኖ እየሰራ ነው።

በአዲስ አበባ እሳትና አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን የአራዳ ቅርጫፍ ጽህፈት ቤት የኦፕሬሽን ዘርፍ ኃላፊ የሆነው ፈቃዱ የሰዎችን ህይወት በታደገባቸው አጋጣሚዎች ችግሮችም አጋጥመውት ያውቃሉ።

በአንድ ወቅት ተከስቶ የነበረን የእሳት አደጋ ሲከላከል በነበረበት ወቅት ሰዎችንና ንብረቶቻቸውን ሲያድን ጣሪያ ተደርምሶ እርሱና ጓዶቹ ጉዳት ያስተናገዱበትን አጋጣሚን አይረሳውም።

በሥራ ቆይታዬ በርካታ የህይወት ማዳን አጋጣሚዎች ስላሉ አደጋን በመከላከል ወቅት የደረሰብኝ ጉዳት ምንም አይመስለኝም ይላል።

በነፍስ አድን ስራ ጉዳት ገጥሞንም ቢሆን የበርካቶችን ህይወት ማዳን በመሆኑ ትልቅ ክብርና ኩራት ይሰማናል፤ ደስተኞችም ነን ብሏል።    


  

የእሳት ነበልባልን ታግሎ ማጥፋት፣ ከተለያዩ አደጋዎች ሰዎችን በማውጣት ህይወታቸውን ማዳን ደስታው ወደር የለውም የሚለው ደግሞ የአደጋ ቁጥጥር ባለሙያው ተመስገን ጳውሎስ ነው።

በሙያችን ሌትም ሆነ ቀን ተዘጋጅተን የምንጠብቀው የሰዎችን ህይወት ከድንገተኛና የእሳት አደጋ ለማዳን በመሆኑ በእኛ ዘንድ ድካም ብሎ ነገር አይሰራም ይላል። 

በመሆኑም ማንኛውም አደጋ ሲከሰት አደጋውን ፈጥኖ በመቆጣጠር ህይወት ለማዳን ሁሌም ዝግጁ ነን ሲል አረጋግጧል።  

"በአደጋ ውስጥ የነበረን ሰው በመታደግ ከጭንቀትና ስቃይ ወጥተው ሲደሰቱ እንደማየት የሚያስደስት ነገር የለም ይላል" የአደጋ ቁጥጥር ባለሙያው ተመስገን።

የኮሚሽኑ የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያ አቶ ንጋቱ ማሞ፤ የሰው ህይወትና ንብረትን የማዳን ስራ የኮሚሽኑ ዋነኛ ዓላማ መሆኑን ይናገራሉ።


 

በመሆኑም አደጋን በመቆጣጠርና የሰዎችን ህይወት ለማዳን በሚደረገው ትግል ህይወታቸውን የሚያጡና ለጉዳት የሚዳረጉ በርካታ የኮሚሽኑ ባለሙያዎች አሉ ብለዋል። 

በዚሁ አጋጣሚ ቁጥራቸው ቀላል የማይባል ሰራተኞች ከከባድ እስከ ቀላል የአካል ጉዳት ማስተናገዳቸውንም ተናግረዋል።

በመሆኑም በእሳት ላይ ተረማምደው የሰው ህይወት የሚታደጉ ጀግኖችን ክብርና ምስጋና ማቅረብ ይገባል ብለዋል።

ጳጉሜን 2 ቀን የመስዋእትነት ቀን ሆኖ "በመስዋእትነት የምትጸና ሀገር " በሚል መሪ ሃሳብ በሀገር አቀፍ ደረጃ በተለያዩ መርሃ ግብሮች ተከብሯል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም