ኢትዮጵያን በቀጣዮቹ 15 ዓመታት የአፍሪካ አቪዬሽን ማዕከል ለማድረግ እየተሰራ ነው- አቶ ደንጌ ቦሩ - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያን በቀጣዮቹ 15 ዓመታት የአፍሪካ አቪዬሽን ማዕከል ለማድረግ እየተሰራ ነው- አቶ ደንጌ ቦሩ
አዲስ አበባ ፤ ጳጉሜ 2/ 2015 (ኢዜአ):-ኢትዮጵያን በቀጣዮቹ 15 ዓመታት የአፍሪካ አቪዬሽን ማዕከል ለማድረግ በቁርጠኝነት እየተሰራ መሆኑን የትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ደንጌ ቦሩ ገለፁ።
በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ የሚቀርበው የአቪዬሽን ኢኖቬሽን ኤክስፖ ከጥቅምት 13 እስከ 17/ 2016 በሳይንስ ሙዚየም ይካሄዳል።
የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለስልጣንና የትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ ሚኒስቴር ኤክስፖውን አስመልክተው መግለጫ ሰጥተዋል::
የትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ደንጌ ቦሩ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ ኢትዮጵያ በአቪዬሽን ዘርፍ የላቀ ውጤቶችን እያስመዘገበች ያለበት ወቅት መሆኑን አንስተዋል::
የዘርፉን ውጤታማነት ወደ ቀጣይ ምዕራፍ ለማሸጋገር እንዲቻልም ተግባራዊ እንቅስቃሴዎች መጀመራቸውን ገልፀዋል።
በዚህም ዘርፉ ላይ በሚጠበቀው ልክ በመስራት በቀጣዮቹ 15 ዓመታት ኢትዮጵያን በአፍሪካ የአቪዬሽን ማዕከል ለማድረግ ውጥን ተይዞ እየተሰራ ነው ብለዋል።
መንግስት በቀጣይም በዘርፉ ላይ ለሚደረጉ ለውጦች ቁርጠኛ ሆኖ ይሰራል ብለዋል።
የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ጌታቸው መንግስቱ በበኩላቸው፤ የኤክስፖውም ዋና ዓላማ በአቪዬሽን የፈጠራ መስክ ላይ ለተሰማሩ ባለሙያዎች እውቅና ለመስጠት መሆኑን ገልጸዋል።
በዚህም የአቪዬሽን ቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን የፈጠራ ባለሙያዎችን በማበረታታትና በመደገፍ በኢትዮጵያ ዘርፉ ወደ ላቀ ደረጃ እንዲሸጋገር ለማስቻል መሆኑን ገልጸዋል።
የአቪዬሽን ሴክተር ዘርፈ ብዙ ሲሆን ኢትዮጵያ በአየር ትራንስፖርት መስክ ያስመዘገበችውን ውጤት በሌሎችም የዘርፉ ሙያዎች ውጤታማና ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ እንድትሆን እየተሰራ ነው።
በኤክስፖ ላይ አየር መንገዶች ፣ አውሮፕላንና ተያያዥ የአቪዬሽን ቴክኖሎጂ አምራቾች፣ በአቪዬሽን አገልግሎት የተሰማሩ የሀገር ውስጥና የውጭ ድርጅቶችና አግባብነት ያላቸው የመንግስትና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች የሚሳተፉ እንደሆነ ተገልጿል።
ድሮንን ጨምሮ የተለያዩ የፈጠራ ውጤቶች ያላቸው ከመላው የሀገራችን ክፍሎች የተወጣጡ የፈጠራ ባለቤቶች የሚሳተፉ ሲሆን በፈጠራ ውጤታቸው ተወዳድረው አሸናፊ ለሚሆኑትን ሽልማት የሚበረከትላቸው ይሆናል ነው የተባለው።
የሲቪል አቪዬሽን ባለስልጣን በባለቤትነት የያዘው ይህ ኤክስፖ የትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ ሚኒስቴር፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ፣ የኢትዮጵያ አየር ኃይል፣ የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር፣ የብሔራዊ አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩትና የስፔስ ሳይንስ ጂኦ ስፓሻል ኢንስቲትዩት ጋር በመተባበር የሚካሄድ ሀገር አቀፍ ኤክስፖ እንደሆነ ተገልጿል።