ለሀገር ዳር ድንበር መከበር መስዋእትነት በመክፈላችን ኩራት ይሰማናል-የቀድሞ የጦር ሰራዊት አባላት - ኢዜአ አማርኛ
ለሀገር ዳር ድንበር መከበር መስዋእትነት በመክፈላችን ኩራት ይሰማናል-የቀድሞ የጦር ሰራዊት አባላት
ቦንጋ፤ ጳጉሜ 2/ 2015 (ኢዜአ):-ለሀገር ዳር ድንበርና ሉዓላዊነት መከበር በከፈሉት መስዋዕትነት ጊዜ የማይሽረው ኩራት እንደሚሰማቸው የቀድሞ የጦር ሰራዊቱ አባላት ገለፁ።
የቀድሞ ጦር ሠራዊት አባላት እንደገለጹት የሃገርን ሉዓላዊነት ለማስከበር በተደረገ ትግል የአካል ጉዳት ቢገጥማቸውም መስዋዕትነቱ የተከፈለው ለተከበረ አላማ በመሆኑ የሚሰማቸው ኩራት በጊዜ ሂደት የማይደበዝዝ ነው ።
የአሁኑ ትውልድ ሀገር በብዙ መስዋእትነት ዛሬ ላይ መድረሷን ሊያውቅና በተለያዩ መስኮች ለሀገሩ ዘብ ሊቆም እንደሚገባም ጠቁመዋል።
የመሰዋእትነት ቀንን አስመልክተው ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉት የቦንጋ ከተማ ነዋሪ የቀድሞ የሀገር መከላከያ ሰራዊት አባላት መካከል ወታደር ወልደሚካኤል ኬቶ አንዱ ናቸው።
በካራማራ ጦርነት ወቅት ለሀገር ሉዓላዊነት መጠበቅ በጦር ግንባር ከጠላት ጋር በነበረ ፍልሚያ የአካል ጉዳት ገጥሟቸው ከጦር ሜዳ መመለሳቸውን ተናግረዋል።
ለሀገር ሉዓላዊነት መከበር በከፈሉት መስዋዕትነት አካላቸው ቢጎድልም ጊዜ የማይሽረው ኩራት ከውስጣቸው ለአፍታ ጠፍቶ እንደማያውቅ ገልጸዋል።
ሀገርን መጠበቅና ወታደር መሆን ከየትኛውም የስራ ድርሻ ይበልጥብኛል ያሉት አስተያየት ሰጪው ቀኑ ህይወታቸውን መስዋዕት የሚያደርጉ የሀገር መከላከያ ሰራዊት አባላትን በማሰብ መከበሩ የሚያስደስት ነው ብለዋል።
ሌላኛው የቦንጋ ከተማ ነዋሪ ወታደር ጌታቸው ክፍሌ ፣ በጦርነት ወቅት የእናት ሀገር ጥሪን ተቀብለው ግንባር በመዝመት በገጠማቸው አደጋ መስዋዕትነት ከፍለው መመለሳቸውን ጠቁመዋል።
"ሀገር እንዲጠበቅ በዱር በገደል መተኪያ የሌለውን ህይወት የሚሰዋ ወታደር ሆኜ በማገልገሌ ለአፍታ የማይጠፋ ኩራትና ደስታ ይሰማኛል" ሲሉ ስሜታቸውን አጋርተውናል።
ከሁሉ በፊት ሀገር መጠበቅ አለበት፤ ሀገር መከበር አለበት፤ ሀገር ከፖለቲካና ከየትኛውም ሀሳብ አይወዳደርም ያሉት አስተያየት ሰጪው ለሀገር ኩራትና ክብር ደግሞ ወጣቱ ሀይል ሀገሩን በዚህ ዘርፍ ተሰማርቶ ሊያገለግል ይገባል ብለዋል።
የሀገር ደጀንና ዋልታ ለሆነው የመከለከያ ሰራዊት ተገቢውን ክብር መስጠት ይገባል ያሉት ወታደር ጌታቸው፣ የአሁኑ ትውልድም ይሄን ተረድቶ በብሄር፣ በቋንቋና በሀይማኖት ከመለያየት ወጥቶ እንደ ሰራዊቱ ለሀገሩ ዘብ መቆም ይገባዋል ብለዋል።
መስዋዕትነት የሚከፈለው በጦር ሜዳ ብቻ አይደለም፤ ሁሉም በየተሰማራበት የሙያ መስክ የግል ጥቅሙን መስዋዕት በማድረግ ሀገርን ከድህነት ለማውጣት በመስራት ወታደር መሆን እንደሚችልም ገልፀዋል።
ሌላኛው አስተያየት ሰጪ የቀድሞ የሀገር መከላከያ ሰራዊት አባል ወታደር ደበበ ሀይሌ በበኩላቸው ሀገርን ከጠላት ለመከላከል የአካል ጉዳት እንደደረሰባቸው ጠቁመው ይህም ለሀገር የተከፈለ በመሆኑ የማይነጥፍ ደስታና ኩራት ይሰማኛል ብለዋል።
ሀገር ከሁሉም በላይ መተኪያ የሌላት ብቸኛ መመኪያ ናት ያሉት ወታደር ደበበ በንፁህ የሀገር ፍቅር ስሜት ከሁሉም ነገር በላይ የሆነችውን ሀገራቸውን ግንባር ድረሰ ሄደው በማገልገላቸው ኩራት ይሰማኛል ነው ያሉት ።
ከመለያየት ይልቅ አንድነትን በማጠናከር በጋራና በተባበረ ክንድ ለሀገር ልማትና ሰላም መስዋእትነት መክፈል የሁሉም ሀላፊነት ሊሆን ይገባል ብለዋል።