የጸጥታና ደህንነት ተቋማት በየትኛውም አጋጣሚ ሀገርና ሕዝብን በማስቀደም በጀግንነት መስዋዕትነት እየከፈሉ ነው-የመከላከያ ሚኒስትር ዴኤታ ማርታ ሊዊጅ - ኢዜአ አማርኛ
የጸጥታና ደህንነት ተቋማት በየትኛውም አጋጣሚ ሀገርና ሕዝብን በማስቀደም በጀግንነት መስዋዕትነት እየከፈሉ ነው-የመከላከያ ሚኒስትር ዴኤታ ማርታ ሊዊጅ
አዲስ አበባ ፤ ዻጉሜን 2/2015 (ኢዜአ) :- የጸጥታና ደህንነት ተቋማት በየትኛውም አጋጣሚ ሀገርና ሕዝብን በማስቀደም በጀግንነት መስዋዕትነት እየከፈሉ መሆኑን የመከላከያ ሚኒስትር ዴኤታ ማርታ ሊዊጅ ተናገሩ።
የመስዋዕትነት ቀን "በመስዋዕትነት የምትፀና ሀገር " በሚል መሪ ሃሳብ በመከላከያ ጠቅላይ መምሪያ ግቢ ተከብሯል።
በመርሃ ግብሩ ላይ መልእክት ያስተላለፉት የመከላከያ ሚኒስትር ዴኤታ ማርታ ሉዊጅ፤ የኢትዮጵያ አርበኞች የሚያስተምሩን የአገር ክብርንና ልዕልና አለማስደፈርን ነው ብለዋል።
በየዘመኑ በጦር ሜዳዎች የተደረጉ ተጋድሎዎች የኢትዮጵያውያንን ፍፁም የሆነ ጀግንነት የሚያረጋግጡ ስለመሆናቸውም አንስተዋል።
በመሆኑም በየትኛውም ጊዜ ኢትዮጵያውያን ለሀገራቸው ክብርና ሉዓላዊነት በጀግንነት መስዋዕትነት በመክፈል ይታወቃሉ ብለዋል።
የጸጥታና ደህንነት ተቋማት በየትኛውም አጋጣሚ ሀገርንና ሕዝብን በማስቀደም በጀግንነት መስዋዕትነት እየከፈሉ መሆኑንም ገልጸዋል።
መከላከያ ሰራዊት ለአገርና ለሕዝብ የተሟላ ሰላም ለማስፈን ፅንፈኞች የለኮሱትን እሳት እያጠፋና በሕዝብና ሀገር ላይ የሚሞከሩ ጥቃቶችን እየመከተ ስለመሆኑም አንስተዋል።
ኢትዮጵያ የረጅም ዘመን ስርዓተ መንግስት መሰረት ያላት በመሆኗ ማንም እየተነሳ ሰላሟን ማናጋት አይችልም ሲሉም ሚኒስትር ዴኤታዋ ተናግረዋል።
የአገር ውስጥ ሰላምና ብሔራዊ ጥቅም ለማስጠበቅ የፀጥታና ደህንነት ተቋማት መገንባት ወሳኝ በመሆኑ በመስኩ ዘርፈ ብዙ የሪፎረም ስራዎች እየተከናወኑ ነው ብለዋል።
ጽንፈኞች የሐሰት መረጃ በመንዛት የተቋማቱን ስም ለማጠልሸት ቢጥሩም አርቆ አስተዋዩ ሕዝብ እኩይ ተግባራቸውን እያመከነ መሆኑን ጠቅሰው የደጀንነት ሚናውን እንዲያጠናክርም ጠይቀዋል።
መስዋዕትነት ከፍለው አገር ያሻገሩ ባለውለታዎችን ማክበርና ማመስገን ይገባልም ብለዋል።