በመስዋዕትነት የምትጸና ሀገር - ኢዜአ አማርኛ
በመስዋዕትነት የምትጸና ሀገር
በመስዋዕትነት የምትጸና ሀገር
በአየለ ያረጋል
የጥንታዊት ሀገር ኢትዮጵያ የሺ-ዘመናት ፍኖት በዘፈቀደ ዛሬ አልደረሰም። የራሷ መልክ እና እሴት ይዛ የመዝለቋ ምስጢር ‘እንደ ዕድል’ አይለም። የታሪክ ሸለቆዎቿ ሲታሰሱ ከቃል የገዘፈ፣ ከአንደበት ያለፈ፣ ከህሊና የከበደ ዋጋና ጥበብ ተከፍሎላታል እንጂ።
በመልክዓ ምድራዊ አቀማመጧ በእሳት ቀለበት የተፈተነች፣ በባንዳዎቿ የተነከሰች፣ በቅርብ እና ሩቅ ጠላቶች በየጊዜው የተዘመተባት ሀገር ናት። የመልክዓ ኢትዮጵያ ዳራ ቢተነተን አያሌ ቁምነገሮች እንደሚኖሩ ዕሙን ነው።
በምድራችን ላይ በርካታ ኅያላን የነበሩ ግዛተ አጼዎች፣ ጥንተ ስልጣኔ መሰረቶች ጠፍተዋል፤ የቀደመ መልክዓ ምድራዊ መሰረታቸው ከስሞ በታሪክ ሕዳግ ላይ ብቻ ቀርተዋል። ኢትዮጵያ ግን የዕልፍ ዘመናት ፈታኝ ውጣ ውረዶችን ተሻግራ ቀጥላለች።
ምጣኔ ሀብታዊ ጉስቁልና ቢጠናወታትም ዳሩ በአኩሪ ታሪክ የከበረች ናት። ጸጋና በረከት ያልተለያት፣ በዓለም ዋቢ ቅርሶቿ የተጌጠች፣ የራሷ ፊደል፣ ትዕምርት እና ትውፊት ጠበቃ ሕልውናዋን ያስቀጠለች ሀገር ናት። የሉዓላዊነቷ እና ሕልውናዋ መጠበቅ ዑደት ውስጥ እንደ ዋስትና የሆኑ የራሷ ዜጎች ዕሴቶች ነበሯት። ከኢትዮጵያ ነባር አሴቶች መካከል አርበኝነትና የሀገር ፍቅር አንዱ ነው።
'መስዋዕት' የሚለው ቃል በባህልም፣ በሃይማኖትም ዐውድ ሲፈተት የፍቅር መገለጫ ጥግ ነው። ራስን ለዓላማ፣ ለፍቅር፣ ለፅድቅ፣ ለአምልኮ… መሰዋት። መስዋዕትነት የሀገር ፍቅር መገለጫ ነው። ለሌሎች ሕልውና የሚከፈል ዋጋ ነው - መስዋዕትነት። ለምሳሌ ‘እናትነት’ የመስዋዕትነት መገለጫ ነው። በዚህ ዐውድ ግን መስዋዕትነትን ከሀገር ሕልውና መቃኘት ይቻላል።
ለሀገር መታመን፣ ለሀገር መሰዋት ትልቅ ክብር ተደርጎ ይወሰዳል። በሀገሬው ተረትም ሆነ በገቢር ከግል አጀንዳ ይልቅ ለሀገር ስቃይና መከራን እስከ ሞት መጎንጨት የጀግንነት እሴት ነው። ኮሎኔል እስጢፋኖስ ገብረመስቀል (የኮሪያ ዘማችና የመጀመሪያው አየር ወለድ ነጻ ዝላይ ያደረጉ መኮንን) ‘ለሀገር የተከፈለ መስዋዕትነት’ በተሰኘው ግለ ታሪካችው “ብዙዎቻችን በአስተዳድጋችን ብቻ ሳይሆን ከዛ ወዲህ የተሰጠን ስልጠና ከሰንደቅዓለማ ጋር የተሳሰረ ነው። በዚህ ሁኔታ በአካልም በመንፈስም የታነጸ ሰው ደግሞ መፈክሩ ’ኢትዮጵያ ወይም ሞት‘ ነው። እኔ በሕይወቴ ያገኘሁት ከፍተኛ ሽልማትና ቁም ነገር አደርጌ የምቆጥረው ህሊናዬ በማይወቅሰኝ መንገድ ሀገሬንና ህዝቤን በማገልገል እዚህ መድረሴ ነው። የእኔ የደስታ ቀናት ብዬ የወሰድኳቸው የአገሬንና ወገኖችን የደስታ ቀናት ነው” ይላሉ።
ኢትዮጵያ በሰማዕታት አጥንት የተማገረች፣ መሬቷ በሰማዕታት ደምና ላብ የለመለመ ነው። በየዘመኑ ምዕናብ የሚመስል ታሪክ ያላቸው የኢትዮጵያ ክብርና ልዕልና ዘብ የቆሙ ሰዎችን መዘርዘር ዓባይን በጭልፋ አይነት ይሆናል።
ለአብነት እንኳ ብናይ በፋሸስት ኢጣሊያ ወረራ ዘመን (ከ1928 እስከ 1933 ዓ.ም) የኢትዮጵያ ጦር በጀግንነት እና ድፍረት የተዋጋበት ታሪክ በቂ ነው። በዚህ ጦርነት የነበረውን የሀገሬው ጀግነነት እና የመስዋዕትነት ጥግ ከኛ ታሪክ ነጋሪዎች ባለፈ በውጭ ፀሐፍት የተጻፉ የዐይን እማኞች በብዛት ከትበውታል።
በዚህ ጦርነት ህልም እንጂ ዕውን የማይመስሉ ጀብዱዎች ተፈጽመዋል። በምድር ያልቻለው ጠላት ግን በዓለም ላይ የተከለከለ መርዝ በአውሮፕላን በመርጨት የዘር ማጥፋት ወንጀል በመፈጸሙ የወገን ሃይል ከባድ መስዋዕትነት ከፍሏል። በተንቤን፣ በሽሬ፣ በአምባራዶም የተሰለፈው የወገን ጦር መርዝ እየጠጣ፣ ሰውነቱ እየቆሰለ፣ ዐይኑ እየታወረ፣ ለአገሩ መስዋዕት ሆኗል። ጠላት አዲስ አበባን ከተቆጣጠረ በኋላ በአምስት ዓመታት ቆይታው ተነግሮ የማያልቅ መልከ ብዙ ጅምላ ጭፍጨፋ አድርጓል። ይህ ግን የሀገሬውን አርበኝነት ወኔ ቀስቅሶ በደም እና አጥንት በተከፈለ መስዋዕትነት ሀገር ድል እንድታደርግ አስችሏል።
የጦርነት ታሪክ ገጾች በበዙባት ኢትዮጵያ መስዋዕትነት ያልነካካው የህብረተሰብ ክፍል የለም። ለኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያዊያን ሉዓላዊነት፣ ነፃነት እና ሕልውና ተጋድሎ አድርገዋል። በሀገር አንድነት እና ሕልውና ላይ የተቃጡ ጥቃቶችን ለመመከት ዋጋ ከፍለዋል።
መስዋዕትነት ራስን ለሌሎች አሳልፎ መስጠት ነው - እስከ ሞት። ለሀገር መስዋዕትነት መክፈል ደግሞ የተለመደ የሕይወት ክስተት ነው። ብዙሃኑ የኢትዮጵያ ሰማዕታት ስማቸው በውል ባይሰፍርም ቁጥራቸው ግን ስፍር ቁጥር የለውም። በጥቅሉ በትውልድ መስዋዕትነት የቀጠለች ሀገር ናት። በተለይም በአርበኝነት ዕይታ፤ በውትድርና ዓለም ለሀገርና ህዝብ ህይወትን መስጠት የተለመደ እሴት ነው። በርግጥ የመስዋዕትነት መገለጫ በጦር ሜዳ ባንዳ እና አርበኛ ብቻ ላይሆን ይችላል። በኑሮ ውስጥም እንዲያው ነው። በብዙ መስክ የሚከፈል መስዋእትነት አለ።
ቀደምት ኢትዮጵያዊያን የግፍ ወረራዎችን አጥንት ከስክሰው፣ ደም አፍስሰው በመታደጋቸው የግዛት አንድነት ከማስጠበቅ ባሻገር ቁሳዊና ኢ-ቁሳዊ ቅርሶቿ እንዲጠበቁ አስችለዋል። የኢትዮጵያዊያን መስዕዋትነት ሀገርን ከወረራ በመታደጉ በዲፕሎማሲው መስክ ሌሎች ያላገኙትን ዕድል እንድታገኝ አስችለዋል።
ድሕረ አድዋ ኢትዮጵያ የጥቁር ሕዝቦች የነጻነት ምልክት ሆና መቀጠሏ፣ የጥቁር አፍሪካዊያን ታሪክና ስልጣኔ ቅርስ መሆኗም ለቅኝ ግዛት አሳቤ አራማጆች መጥፎ ስሜት ማሳደሩ አልቀረም። ለሀገሬው ኩራት፣ ለታሪክ ክብር እና ለሌሎቸም የትግል ፋና ወጊ አድርጓታል። ኢትዮጵያ በታሪክ ምዕራፏ የትልቅ ሀገርነቷ ሕያው ምስከር ቅርሶች አሏት።
እንድትፈራርስ የምንጊዜም ፍላጎታቸው የሆኑ አካላት በየዘመኑ ወደ ገደል ሲገፏት ቢኖሩም በልጆቿ ሰማዕትነት ነው ተከብራ የኖረችው። ሉዓላዊነቷን አስጠብቃ መቆየት ብቻ ሳይሆን ለሌሎች ህዝቦች ነጻነት፣ ሰላምና መረጋጋት በበርካታ አገሮች በተጫወተችው ሚናም ለአፍሪካ ህብረትና ለሌሎች ዓለም አቀፍ ተቋማት ማዕከል መሆን አስችሏታል።
የመስዋዕትነት እርሾዎች - የትውልድ መልክ
ትውልድ ገንቢዎችን ይመስላል። ከቀዳሚዎቹ ውርሱ፣ ለተከታዮቹ ቅርሱ የሚያነብረው አሻራው ዘመኑን የሚዋጅ ነው። የመስዋዕትነት እሴት ያዳበረ ትውልድ የሀገር ፍቅር መገለጫ ማህተም ነው።
በሰዎች ማንነት ቀረጻ ዙሪያ “ሰዎች ሲፈጠሩ የሰውየውን ችሎታ ይዘው ነው ወይስ የሰዎች ማንነት የሚቀረጸው ከውልደት በኋላ በተሞክሮ ወይም ከአካባቢ ጋር በሚኖራቸው መስተጋብር ነው” የሚሉ ምሁራዊ ሃሳቦች ይነሳሉ። በየትኛውም የክርክር መደብ ዜጋ እና ትውልድ ቀራጺውን ይመስላል።
ዶክተር ይሁኔ አየለ ‘እናት’ በተሰኘ መፅሃፋቸው “የእናት ሀገር ህልውና ከእናቶች ሕይወት ጋር በቀጥተኛ ተዛመዶ አለው። የሠመረ ትውልድ ሊቀጥል የሚችለው በጥሩ ሁኔታ በተገነባ የእናቶች አቅም ነው። የእናቶች አቅም ሲገነባ የራሳቸውን አቅም ያውቃሉ፤ ምርጫቸውን በራሳቸው ይወስናሉ፤ እንዲሁም ለሚመጣው ማህበራዊ ለውጥ የራሳቸውን አሻራ ያሳርፋሉ። ስለሆነም የእናቶችን አቅም ማጎልበት ትውልድን ማጎልበት ነው። እናቶች ላይ መስራት ትውልድ ላይ መስራት ነው” ይላሉ።
የሀገርን ታሪክ ያወቀና የተረዳ ትውልድ ለጽኑና አይበገሬ ሀገር ግንባታ እንደሚበጅ፣ ለመስዕዋትነት እንደሚዘጋጅ ዕሙን ነው። ታሪክና ሀገሩን የሚያውቅ ትውልድ ሲገነባ ሀገር ይጸናል። በሀገር ፍቅርና ትውልድ ግንባታ ላይ አበክሮ የሚጎተጉተው ኢያሱ በካፋ (ነፍስ ይማር) “ሀገር እና ዜግነት“ በተሰኘው መጣጥፉ ዜጎቻችን ስለሀገራችን ታሪክ፣ ስለአርበኞቻችን ጀግንነት፣ ስለመስዋዕትነታቸው፣ ስለ ሊቆቻችን ይበልጥ ባወቁ ቁጥር ሀገራቸውን እያፈቀሩ፣ ይበልጥ አርበኛ፣ ይበልጥ ጀግኖች፣ ይበልጥ ሊቆች እንደሚሆኑ ያትታል።
አገርን ለጥፋት ከሚዳርጉ አስተሳሰቦች የጸዳ እንዲሁም ከሙሰኝነት የነጻ ትውልድ መገንባት ያሻል። ፍትህና ርትዕ ማስፈንም እንዲሁ ግድ ይላል። በሙስና የነቀዘ ትውልድ በራስ መተማመን አይኖረውም። ፍትህ ርትዕ ከሰፈነ ግን ብሩህ፣ አዲስ ሃሳብና ሃይል አፍላቂ እንዲሁም ለሀገሬ ምን ሰራሁ የሚል ትውልድ ይፈጠራል። ከኢያሱ በካፋ ገለጻ ሰናይ ምግባር ከአርበኝነት፤ እኩይ ምግባር ደግሞ ከሙሰኝነት፣ ራስ ወዳድነት፣ ዘረኝነት፣ አድሏዊነት፣ ቀናተኝነት፣ ተንኮለኝነት፣ ድንቁርና ጨካኝነት ጋር የሚተሳሰር ነው።
በአጭሩ የትውልድ መልክ የሀገረን ዕጣ ፈንታ ይወስናል። በመስዕዋትነት የተረከቧትን ኢትዮጵያ ለመጠበቅና ለማሳደግ በመልካም ምግባር የተገነባና በሀገር ፍቅር የተቃኘ ትውልድ ያሻል። ከሕልውና መጠበቅ ባለፈ የበለጸገና ያደገ ሀገር ለመገንባት ሁነኛ ዋስትና ይሆናል። ‘የአገልጋይነት ቀን፣ የመስዋእትነት ቀን፣ የበጎነት ቀን፣ የአምራችነት ቀን፣ የትውልድ ቀን፣ የአብሮነት ቀን’ ሲወሳ ልብ መባል ያለበት ይሄው ነው -ትውልድ ግንባታ። ምክንያቱም በቅጡ የተገነባ ትውልድ ያመርታል። በበጎነትና ቀናኢነት የተኮተኮተ ትውልድ በአግባቡ ያገለግላል።
በትውልድ ቅብብሎሽ መሻገርና መወረስ ያለባቸውን ነባር ኢትዮጵያዊ እሴቶች መኮትኮት፣ ማጎልበትና ማውረስ ይጠይቃል።
የሀገር ፍቅርና አርበኝነት
የሀገር ፍቅር በልብ የሚታተም ጥልቅ ስሜት፣ የእኔነት ስነ ልቦና ነው። ይህ ደግሞ ለሀገር፣
ለወገን ራስን አሳልፎ ለመስጠት መሰረት ነው። ሀገርን ለመታደግ በእምነትና በፍቃድ ለመዝመት የሀገር ፍቅር ይጠይቃል።
ሀገር የባህል፣ የሀብት፣ የወግ፣ የቋንቋ፣ ወይም የሌላ ማንነት የወል ስሪት ነው። የሀገር ፍቅር ከራስ ጥቅም ይልቅ የህዝቡን ጥቅም ማስቀደም፤ ለፍትሃዊነት መገዛት፣ ከራስ ወዳድነት መራቅ ነው። ለሀገር ገጽታ መጉደፍ መጨነቅ፣ ለተፈጥሯዊና ታሪካዊ ሃብቶች መቆርቆር፣ ለብሔራዊ ጥቅም መቆም የሀገር ፍቅር ነው።
ቅደመ አድዋ እና ድሕረ አደዋ የውጭ ወራሪ ኃይል ጋር በተደረገ መዋደቅ አያት ቅድመ አያቶቻችን የከሰከሱት አጥንትና ያፈሰሱት ደም የሀገር ፍቅር ውጤት ነው። ኢትዮጵያ በየዘመኑ ሀገርንና ወገንን በሆድ የለወጡ ቡድኖችና ግለሰቦች ቢፈትኗትም የሀገር ፍቅርና አርበኝነት እሴት ባላቸው ልጆቿ ግን አርነቷን አረጋግጣለች።
የነዚህ ጀግኖች ድል ሲታሰብ ደግሞ አብሮነት የወል ማስተሳሰሪያ ሆኖ ይነሳል። ኢትዮጵያ የጸናቸው በሁሉም ማዕዘናት ባሉ ልጆቿ የጋራ መስዋዕትነት ነውና። አብሮነት ለኢትዮጵያ ሕልውና ምን ያህል እንደበጀ በብዙ አተያይ መመልከት ይቻላል። አደዋን ማንሳት ከበቂ በላይ ነው። የታሪክና ፍልስፍና ምሁራን እንደሚሉት አድዋ በታሪክ ኢትዮጵያዊያን ብሔር፣ ጾታ፣ ሃይማኖት፣ ማህበራዊ መደብ እና ቅራኔ እና ልዩነት ሳይበግራቸው ድርና ማግ ሆነው በአብሮነት እና አንድነት ዘመቱ። ድልም ነሱ። አንድነትና አብሮነት እሴቶች ባይኖሩ ኖሮ ሀገር በመስዕዋትነት ላትፀና ትችል ነበር።
ሀገር የአንድነት ማህበር ቤት ናት። ኢትዮጵያ በታሪኳ ባለፈቻቸው ውጣውረዶች ሁሉ ዋጋ ተከፍሏል፤ የሚደንቅ ዋጋ። ይህ ትውልድ ይህችን ዕልፍ ትውልድ ዋጋ ከፍሎ ያሻገራትን ታሪካዊት ሀገር ጠብቆ ከተረከበው አልቆ ማስረከብ ይገባዋል። ኢትዮጵያ በርግጥም በመስዋዕትነት የምትጸና ሀገር ናት። እናም ትውልዱ በተሰማራበት ሁሉ የሚጠበቅበትን ለሀገር በመክፈል ኢትዮጵያን የበለጠ ማጽናት ይጠበቅበታል።