ቀጥታ፡

ሀገራችን የሚገጥማትን ፈተና ለመሻገር ዋጋ የምንከፍል ሠራዊት በመሆናችን ልንኮራ ይገባል--ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገብረሚካኤል

አዲስ አበባ ፤ ጳጉሜን 2/2015 (ኢዜአ)፡- ሀገራችን የሚገጥማትን ፈተና ለመሻገር ከሌሎች የፀጥታ ተቋማት ጋር በቅንጅት ዋጋ የምንከፍል ሠራዊት በመሆናችን ልንኮራ ይገባል ሲሉ የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገብረሚካኤል የወቅቱ የምስራቅ አፍሪካ ፖሊስ አዛዦች ህብረት ድርጅት ፕሬዚዳንት ገለጹ።

"በመስዋዕትነት የምትፀና ሀገር '' በሚል መሪ ሀሳብ የመስዋዕትነት ቀን በኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ዋናው መስሪያ ቤት ተከብሯል።

በመርሃ ግብሩ ላይ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገብረሚካኤል የወቅቱ የምስራቅ አፍሪካ ፖሊስ አዛዦች ህብረት ድርጅት ፕሬዚዳንት የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ከሌሎች የፀጥታ ተቋማት ጋር ተቀናጅቶ በሀገራችን በሁሉም ማዕዘናት የህይወት መስዋዕትነት እየከፈለ ሀገራችንን ከማንኛውም የፀጥታ ችግሮች እየታደገ ይገኛል ብለዋል።

ቀኑ ሲከበር የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ሠራዊት ውድ ህይወቱን መስዋዕት እያደረገ ሀገርን በማፅናት ዛሬ ላይ ማድረሱንም ገልፀዋል።

ለሰው ልጅ ከባዱ ነገር ውድ ህይወቱን አሳልፎ መስጠት መሆኑን ያነሱት ኮሚሽነር ጀነራሉ የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ አመራርና አባላቱ ለዜጎችና ለሀገር ደህንነት እራሳቸውን አሳልፈው እየሰጡ መሆኑን ተናግረዋል።

የመስዋዕትነት ቀን መታሰቢያ ዛሬ ብቻ ተከብሮ የሚያበቃ ባለመሆኑ ወደ ፊትም ሀገራችን የሚገጥማትን ፈተና ለመሻገር ከሌሎች የፀጥታ ተቋማት ጋር በቅንጅት ዋጋ የምንከፍል የሀገር ባለውለታ ሠራዊት በመሆናችን ልንኮራ ይገባል ብለዋል።

ኮሚሽነር ጀነራሉ እንደዚህ አይነት ፕሮግራሞች ሲዘጋጁ ያለፉ ሰማዕታትን የምናስታውስበትና እኛም በቀጣይ ለሀገራችን መስዋእትነት ለመክፈል የምንዘጋጅበትና የሀገራችንን ፖሊስ በከፍተኛ ደረጃ አቀናጅተን የተሻለ ፖሊሳዊ አገልግሎት የምንሰጥበት ነው ሲሉ ገልጸዋል።

በተጨማሪም የህግ የበላይነት እንዲረጋገጥ፣ ዜጎች በሰላም ወጥተው የሚመለሱበት፣ የሀገር ልማት የሚፋጠንበት ቃላችንን በድጋሜ የምናድስበት ዕለት ስለሆነ ሁላችንም በአንድነት ለሀገር ዘብ እንደምንቆም በመተማመን የምናከብረው በዓል ነው ማለታቸውን ከፌዴራል ፖሊስ የተገኘው መረጃ ያመላክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም