ቀጥታ፡

የመጀመሪያው የአቪዬሽን ኢኖቬሽን ኤክስፖ የፊታችን ጥቅምት በሳይንስ ሙዚየም ይካሄዳል

 አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 2/2015 (ኢዜአ)፦ የመጀመሪያው የአቪዬሽን ኢኖቬሽን ኤክስፖ የፊታችን ጥቅምት 13 እስከ 17 በሳይንስ ሙዚየም እንደሚካሄድ ተገለጸ።

የትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ ሚኒስቴርና የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለስልጣን ኤክስፖውን አስመልክቶ  መግለጫ ሰጥተዋል::

ኤክስፖው "የአቪዬሽን ኢኖቬሽን ለላቀ ተወዳዳሪነት" በሚል መሪ ቃል የሚከናወን ነው።

የትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ደንጌ ቦሩ ኢትዮጵያ በአቪዬሽን ዘርፉ የላቀ ውጤት እያስመዘገበች ትገኛለች ብለዋል።

በቀጣይ የዘርፉን ውጤታማነት ወደ ቀጣይ ምዕራፍ ለማሸጋገር የሚያስችል ስራ ለማከናወን እንቅስቃሴ እየተደረገ መሆኑን አመልክተዋል።

በመጪው ጥቅምት ወር ይፉ የሚሆነው ይህ ኤክስፖም   በአቪዬሽን ፈጠራ ላይ የተሰማሩ ባለሙያዎችንና ልዩ ልዩ አካላትን እውቅና በመስጠት በመደገፍና በማበረታታት የአቪዬሽን ቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን እንዲስፋፋ ማድረግ ነው ብለዋል::

መንግስት በቀጣዮቹ 15 አመታት ኢትዮጵያን በአፍሪካ የአቪዬሽን ማዕከል ለማድረግ ውጥን ይዞ እየሰራ መሆኑን ነው ሚኒስትር ዴኤታው የገለጹት።

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም