ቀጥታ፡

መሰዋዕትነት ከፍሎ አገርን ከማስቀጠል በላይ ትልቅ እርካታ የሚሰጥ ተግባር የለም --- ከፍተኛ መኮንን፣ የጸጥታ አባላትና ኃላፊዎች

 ነቀምት/ጎባ ፣ጳጉሜን 02/2015 (ኢዜአ)፡- አስፈላጊውን መሰዋዕትነት ከፍሎ አገርን ከማስቀጠል በላይ ትልቅ እርካታ የሚሰጥ ተግባር የለም ሲሉ የምዕራብ እዝ ከፍተኛ መኮንንና ሌሎች የጸጥታ አባላትና ኃላፊዎች ተናገረ።

ጳጉሜን 2 የመስዋዕትነት ቀን በመላው ኢትዮጵያ “በመስዋዕትነት የምትጸና ሀገር” በሚል መሪ ሃሳብ በተለያዩ መርሐ ግብሮች እየተከበረ ነው።

ቀኑን አስመልክቶ ኢዜአ ያነጋገራቸው የምዕራብ እዝ ከፍተኛ መኮንንና ሌሎች የጸጥታ አባላትና ኃላፊዎች መስዋዕትነት ከፍሎ አገርን ከማስቀጠል በላይ ትልቅ እርካታ የሚሰጥ ተግባር የለም ይላሉ።

በአገር መከላከያ ሰራዊት የምዕራብ እዝ ከፍተኛ መኮንን የሆኑት ኮለኔል ሲራጅ ሲምቢሩ፣ ለሰላሳ አመታት በሰራዊት አባልነት ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ ሀገራቸውን ማገልገላቸውን ገልጸው የሀገር ሉዓላዊነትን ማስጠበቅ መሰዋእትነት ይጠይቃል ብለዋል።

የሀገር መከላከያ ሰራዊት በየቀኑ ህይዎቱን እየገበረ፣ ለአካሉ ሳይሳሳ ሀገሩን ቤተሰቡ አድርጎ የአገር ሉዓላዊነትን እያስከበረ መሆኑንም ተናግረዋል።

‘’ህዝባችን በሰላም ወጥቶ እንዲገባ፣ ልማት እንዲቀጥል የሀገር መከላከያ ሰራዊትና ሌሎች የጸጥታ አካላት መስዋእትነት እየከፈሉ ነው'' ብለዋል።

እስቸው ባሉበት አካባቢም የሀገረ መከላከያ ሰራዊትና ሌሎች የጸጥታ አካላት የህዝቡን ሰላም ለማረጋገጥ መስዋዕትነት እየከፈሉ መሆኑን አስታውሰዋል።

በዚህ ሁሉ መስዋዕትነት ውስጥ የህዝብ ድጋፍ እና አብሮነት ደግሞ የመከላከያ ሰራዊትን የበለጠ እያጸናው ለተጨማሪ መስዋዕትነት እንዲዘጋጅ እያደረገው ነው ብለዋል።

በአዲሱ አመትም እሳቸው ያሉበት የሰራዊት ክፍል የአገር ሉዓላዊነትንና የህዝቡን ደህንነት ለማረጋገጥ በመስዋዕትነት ይቀጥላል ሲሉም አረጋግጠዋል።

ኮለኔሉ የአገርን ዳር ድንበርና ሉዓላዊነት ለማስከበር ከሚከፈል መስዋዕትነት በላይ ትልቅ ተግባር ባለመኖሩ ለአገራቸው አስፈላጊውን መስዋዕትነት መክፈሉን እንደሚቀጥሉ አረጋግጠዋል።

የጸጥታ አካላት ለሕግ የበላይነት መከበር በጀግንነት የሚያደርጉት ተጋድሎ ነጻነትን የተጎናጸፈች አገርን ለትውልድ ማሻገር ያስቻለ መሆኑን ደግሞ ሌሎች የጸጥታ አካላት ይናገራሉ።

 

በ1990ዎቹ መጀመሪያ በሰሜን ኢትዮጵያ በተካሄደ ጦርነት ለአገሩ ሉዓላዊነት መከበር ባደረገው ተጋድሎ ጉዳት እንደደረሰበት የሚናገረው የቀድሞ ወታደር አስር አለቃ ወሰንዬለህ ኪዳኔ፤ መስዋዕትነት ለአገር ክብር የሚከፈል ዋጋ ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ የጸጥታ አካላት በአገር ላይ የሚቃጡ ወረራዎችና ትንኮሳዎችን በጀግንነት የሚቀለብሱና ድል የሚያሰመዘግቡ የአንድነት አምድና የሉዓላዊነት ምሰሶ ናቸው ሲሉም ተናግረዋል፡፡ 

አስር አለቃ ወሰንየለህ ኪዳኔ፤ የመከላከያ ሰራዊትና ሌሎች የፀጥታ አካላት ዛሬም እንደትናንቱ በአገር ላይ የሚቃጡ የውስጥና የውጭ ትንኮሳዎችንና ወረራዎችን በመመከት ድል ማድረጉን መቀጠሉን አንስተዋል።

ህዝቡም ነጻነቷን የተጎናጸፈች አገርን ለትውልድ ማሻገር እንዲቻል መስዋዕትነት ከሚከፍለው የጸጥታ አካላት ጎን በመሆን ትብብርና ተሳትፎውን አጠናክሮ መቀጠል አለበት ብለዋል፡፡  

 

የባሌ ዞን ፖሊስ መምሪያ አዛዥ ምክትል ኮሚሸነር ጄይላን አማን በበኩላቸው፤ የፖሊስና ሌሎች የፀጥታ አካላት የብሔራዊ አንድነት መገለጫ በመሆናቸው ትልቅ ክብር ሊሰጣቸው እንደሚገባ ገልጸዋል። 

ለአገር ሉዓላዊነትና የግዛት አንድነት የሚከፈል መስዋዕትነት ክብር መሆኑን የገለጹት ምክትል ኮሚሸነሩ፤ በተለይም ለፖሊስ አባላት ይህንኑ ተግባር ማጠናከር አለባቸው ብለዋል። 

ምክትል ኮሚሽነሩ እንዳሉት፣ የዞኑ ፖሊስ መስዋዕትነት ቀንን ሲያከብር ለአገር ክበር፣ ለህዝብ ሰላምና ደህንነት የገባውን ቃል ኪዳን በብቃት ለመፈፀም በመዘጋጀት መሆኑንም ተናግረዋል። 

የመስዋዕትነት ቀን መከበሩ የጸጥታ አካሉ የተሰጠውን ተልዕኮ ከመቼውም ጊዜ በላይ ለማሳካት ለሚደረገው ጥረት ተጨማሪ አቅም ይሆና ያሉት ደግሞ የባሌ ዞን የፀጥታና አስተዳደር ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አሸናፊ ወለደዮሃነስ ናቸው፡፡

"መስዋዕትነት የጀግንነት፣ የጽናትና የአሸናፊነት ውጤት ነው" ያሉት አቶ አሸናፊ፤ ሁሉም በተሰማራባት ዘርፍ በጀግንነት መስዋዕትነት በመክፈል ኢትዮጵያን ለማሻገር በሚደረገው ጥረት ውስጥ አሻራውን ሊያኖር ይገባል ብለዋል።

የዞኑ የሚሊሻ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አብዱልቃድር ኡስማን በበኩላቸው፤ በዞኑ የሚገኙ ሁሉም የጽጥታ አካላት ባለፉት አራት ዓመታት በቅንጅትና በትብብር በሰሩት የተቀናጀ ሥራ በዞኑ የተሻለ ሰላም እንዳለ ተናግረዋል ተናግረዋል፡፡

በዚህም ህዝቡ የለምንም የጽጥታ ሥጋት ወጥቶ በመገባትና በልማቱ ላይ በመበርታት አመርቂ ውጤት እያሰመዘገባ መሆኑን ለዚሁ ጥረት ማሳያ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በመሆኑም ኢትዮጵያውያን ለሰላምና አብሮነታቸው መረጋገጥ ሲሉ በጀግንነት ለአገራቸው መስዋዕትነት ለሚከፍሉ በየደረጃው ለሚገኙ የጸፀጥታ አካላት ጎን እንዲቆሙ ጠይቀዋል፡፡

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም