ቀጥታ፡

የመስዋዕትነት ቀን በተለያዩ መርሐ-ግብሮች እየተከበረ ነው 

አዲስ አበባ፤ ጳጉሜን 2/2015 (ኢዜአ)፦የመስዋዕትነት ቀን "በመስዋዕትነት የምትጸና አገር" በሚል መሪ ሃሳብ ደም ልገሳን ጨምሮ በተለያዩ ሁነቶች በአዲስ አበባ በመከበር ላይ ነው።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እለቱን አስመልከቶ ከተለያዩ የጸጥታ ተቋማት ጋር ውይይት በማካሄድ ላይ ይገኛል።

የአገር መከላከያ ሰራዊት፣ የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ፣ የአዲስ አበባ ፖሊስ፣ የደንብ ማስከበርና የሕዝባዊ ሰራዊት አባላትና አመራሮች በመድረኩ ላይ ተገኝተዋል።

የከተማ አስተዳደሩ ሰላምና ጸጥታ ቢሮ ኃላፊ ሊድያ ግርማ፤ ለኢትዮጵያ የተከፈለውንና እየተከፈለ ያለውን መስዋዕትነት በመዘከርና ተገቢውን ክብር በመስጠት ቀኑ እየተከበረ መሆኑን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያን ለማጽናት የተከፈለውንና እየተከፈለ ያለውን መስዋዕትነት በቅጡ በመረዳት ሁላችንም ተገቢውን ክብርና እውቅና መስጠት ይገባናልም ብለዋል።

ኢትዮጵያ  በዜጎቿ እና በጀግኖች የጸጥታ ሃይሎች መስዋእትነት ክብሯና ሉአላዊነቷ ተጠብቆ መቆየቱን ጠቅሰው የአሁኑ ተውልድም ይህንኑ ማስቀጠል ይጠበቅበታል ነው ያሉት።

የጳግሜን 2 የመስዋእትነት ቀን "በመስዋእትነት የምትጸና ሀገር " በሚል መሪ ሃሳብ በመላ ሀገሪቷ በተለያዩ መርሃ ግብሮች በመከበር ላይ ይገኛል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም