የመስዋዕትነት ቀን መዘከሩ ለሠራዊቱ ኩራትን በማጎናፀፍ ይበልጥ ለሃገሩ መስዋዕትነትን እንዲከፍል ያነሳሳል-የደቡብ ዕዝ ጠቅላይ መምሪያ አባላት - ኢዜአ አማርኛ
የመስዋዕትነት ቀን መዘከሩ ለሠራዊቱ ኩራትን በማጎናፀፍ ይበልጥ ለሃገሩ መስዋዕትነትን እንዲከፍል ያነሳሳል-የደቡብ ዕዝ ጠቅላይ መምሪያ አባላት
ሐዋሳ፤ጳጉሜን 2/2015 (ኢዜአ)፦በሀገሪቱ የመሰዋትነት ቀን መዘከሩ ለሠራዊቱ አባላት ታላቅ ኩራትን በማጎናጸፍ ይበልጥ ለሀገሩ መሰዋእትነትን እንዲከፍል የሚያነሳሳ ነው ሲሉ በኢፌድሪ መከላከያ ሚኒስቴር የደቡብ ዕዝ ጠቅላይ መምሪያ አባላት አስታወቁ።
የእዙ አባላት እንደሚሉት ዛሬም እንደ ጥንቱ የአባቶቻቸውን ወደር የሌለው ጀግንነትና የሀገር ፍቅርን በማስቀደም ለሀገራቸው መስዋእትነት ለመክፈል ዝግጁነታቸውን አረጋግጠዋል።
በደቡብ ዕዝ ጠቅላይ መምሪያ የሥነ ልቦና ግንባታ ዳይሬክተር ኮሎኔል ወንድወሰን አስፋው ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ እንዳሉት የዘንድሮውን ዻጉሜን 2 በመስዋእትነት ቀን መዘከሩ ለመላው የሠራዊት አባላት ክብር ከማጎናጸፉም ባሻገር የሰራዊቱን መንፈስ የሚያድስ ነው።
መከላከያ ሠራዊት ለሀገሪቱ ሉዓላዊነት መከበርና ዳር ድንበር መጠበቅ ሲል ከፍተኛ መስዋእትነት እየከፈለ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
በተለይ አሁን ላይ ህገ መንግስታዊ ሥርዓቱን የሚገዳደሩ ፀረ ሠላም ኃይሎችን በመመንጠር በሀገሪቱ አስተማማኝ ሠላም ለማስፈን ውድ ህይወቱን እየከፈለ መሆኑን ጠቅሰዋል።
ይህ ሠራዊት ለኛ ብሎ ነው መሰዋትነት እየከፈለ ያለው ብለው የኢትዮጵያ ህዝቦች ዻጉሜ ሁለትን ሲዘክሩ ለሰራዊቱ ትልቅ ኩራት የሚሰጥ ነው ሲሉ አውስተዋል።
የበለፀገችና ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን ለማየት ካለን ፅኑ ፍላጎት የተነሳ ሀገራችንን በደምና በአጥንት ከጠላት በመጠበቅ ህዝባችንን የሚያኮራ ገድል በመፈጸም ያልተደፈረች ሀገር ለመጪው ትውልድ ለማስረከብም ይበልጥ እንድንነሳሳ የእለቱ መዘከር ፋይዳው የጎላ ነው ብለዋል።
በወጣትነታቸው ሰራዊቱን በመቀላቀል ለ30 ዓመታት በጀግንነት ማገልገላቸውን የሚናገሩት ኮሎኔል ወንድወሰን የአሁኑ ትውልድ ውትድርና ሙያ መሆኑንና ሀገርን መጠበቅ ኩራት እንደሆነ በመገንዘብ ሠራዊቱን ተቀላቅሎ ሀገሩን እንዲያገለግል መልእክት አስተላልፈዋል።
በመምሪያው የኮርዲናንስ ኃላፊ ሌተናል ኮሎኔል ሰኢድ ሁሴን በበኩላቸው የመስዋእትነት ቀን መሰየሙ ለሰራዊቱ ትልቅ ስንቅና ሞራል እንደሚሆነው ጠቁመዋል።
እለቱን ስንዘክር ለሀገር ዳር ድንበር ዘብ የሚቆም ትውልድ መፈጠር እንዳለበት በመስራት ሊሆን እንደሚገባም አመላክተዋል።
የኢትዮጵያ ልጆች የአጥንትና የደም መሰዋእትነት ከታሪክ ማህደር የማይጠፋ ስማቸው ከመቃብር በላይ ሆኖ ሲዘከር ይኖራል ያሉት የጦር መኮንኑ ትውልዱ ታሪኩን ማሰቀጥል እንዳለበት አስገንዝበዋል።
በተለያዩ ግዳጆች መሳተፋቸውን ጠቅሰው ለሀገር ክብር ሲባል በመቁሰላቸውና መስዋእትነት በመክፈላቸውም ታላቅ ክብር እንደሚሰማቸው ተናግረዋል።
መከላከያ ሠራዊት ኢትዮጵያን ከሀገር ውስጥና ከውጭ ጠላቶቿ ለመታደግ፣ ነፃነታችንን አሳልፎ ላለመስጠት፣ ብርቱ ክንዱን በማሳረፍ አኩሪ መሰዋእትነት የከፈለ ግዙፍ ተቋም መሆኑን የምትናገረው ደግሞ የዕዙ አባል ምክትል አስር አለቃ ፋናዬ ታደሰ ናት።
ሠራዊቱ ከራስ በፊት ለህዝብና ለሀገር ብሎ የሚሰራና የሚታገል ስለሆነ ክብር ይገባዋል የምትለው አስር አለቃ ፋናዬ ባለፉት ስምንት ዓመታት በውትድርና ህይወቷ ደስታ እንደሚሰማት ትናገራለች።
በውጊያ ጊዜ ብዙ ውጣ ወረዶችን ከማሳለፍ ባለፈ ቆስዬ አይቻለሁ የምትለው ፋናዬ በተለይ አዋጊ አመራሮች በቆሰሉ ጊዜ የሬድዮ መገናኛ በማንሳትና እነሱን በመተካት ኃይሉን በማስተባበር ከጋንታ መሪ እሰከ ሻለቃ መሪ በማዋጋት ጀብዱ መፈፀሟን አውስታለች።
በዚህ ጀግንነቷም ከፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴና ከደቡብ ዕዝ ጠቅላይ መምሪያ ሽልማትና የወርቅ ሜዳለያ እንደተበረከተላት አብራርታለች።
በውትድርና ሙያ እስከ መጨረሻው በጡረታ እስከምትሰናበት ድረስ በማገልገል ታሪካዊ ግዴታዋን ለመወጣትና ለመጪው ትውልድ ለማስረከብ ቆርጣ መነሳቷንም አስታውቃለች።
አገር እናት ናት፣ሁሉ ነገር ናት የምትለው አስር አለቃ ፋናዬ በመሆኑም ወጣቶች የውትድርና ሙያን አክብረው በመቀላቀል የአኩሪ ታሪክ ባለቤት እንዲሆኑ ጠይቃለች።