ቀጥታ፡

በሁሉም መስክ ለሀገራቸው መስዋእትነት የከፈሉ ጀግኖችን ማክበር፣ ማመስገንና ተገቢውን ክብር መስጠት ይገባል- አትሌት ቀነኒሳ በቀለ

አዲስ አበባ፤ ጳጉሜን 2/2015(ኢዜአ)፦ በሁሉም መስክ ለሀገራቸው መስዋእትነት የከፈሉ ጀግኖችን ማክበር፣ ማመስገንና ተገቢውን ክብር መስጠት ይገባል ሲል ጀግናው አትሌት ቀነኒሳ በቀለ ተናገረ።

ኢትዮጵያ በዓለም መድረክ ለክብሯ ከፍታ፣ ለስምና ገጽታዋ ድምቀት በየሙያ መስኩ አኩሪ ገድል የፈጸሙና መስዋዕትነት የከፈሉ በርካታ ጀግኖች አሏት።

በስፖርቱ ዓለም ብንመለከት በባዶ እግሩ በመሮጥ ኢትዮጵያን ባለድል ካደረገው ሻምበል አበበ ቢቂላ እስከ ማርሽ ቀያሪው ምሩፅ ይፍጠር መጥቀስ ይቻላል።

ከፋጡማ ሮባ እስከ ደራርቱ ቱሉ፣ ከኅይሌ ገብረሥላሴ እስከ ቀነኒሳ በቀለ፣ ጥሩነሽ ዲባባ፣ መሰረት ደፋር እና ሌሎችም ለሀገራቸው በጀግንነት ታሪክ የሰሩ አትሌቶች ይጠቀሳሉ።

ኢትዮጵያ ሰንደቋ እንዲውለበለብ፣ ህብረ ዝማሬዋ እንዲሰማና ስሟ እንዲናኝ አበርክቶ ከነበራቸው ድንቅ አትሌቶች መካከል በረጅም ርቀት ውድድሮች በአሸናፊነቱ ዓለምን ያስደመመው ጀግናው አትሌት ቀነኒሳ በቀለ ይጠቀሳል።

የብዙ ክብረ ወሰኖች ባለቤት፣ የበርካታ ሜዳሊያዎች አጥላቂ፣ በአሯሯጥ ስልቱ አስደማሚው ቀነኒሳ በቀለ፤ በተሰለፈባቸው ውድድሮች ሁሉ የሀገር ኩራት ከመሆን ባለፈ የዓለም የውድድር ድምቀት መሆኑ ይታወቃል።

በኦሎምፒክ የሶስት ወርቅ፣ በዓለም ሻምፒዮና አምስት ወርቅ፣  በዓለም የቤት ውስጥ አትሌቲክስ ሻምፒዮ አንድ ወርቅ፣ በአፍሪካ አትሌቲክስ ሻምፒዩን 2 ወርቅ፣ በመላው አፍሪካ ጨዋታዎች ሁለት ወርቅ፣ በዓለም አገር አቋራጭ 11 የወርቅ ሜዳሊያ እና በበርሊን ማራቶን እኤአ በ2016 እና በ2019 ሁለት የወርቅ ሜዳሊያ መውሰድ የቻለ ድንቅ አትሌት ነው።

በዓለም አቀፍ ውድድሮች በድምሩ 26 የወርቅ ሜዳሊያዎችን በማግኘት የዓለም የውድድር ድምቀትና የኢትዮጵያ ኩራት መሆን ችሏል።

ጀግናው አትሌት ቀነኒሳ በቀለ ከኢዜአ ጋር በነበረው ቆይታ ኢትዮጵያ ከአትሌቲክስ በተጨማሪ በሁሉም የሙያ መስክ በርካታ ጀግኖችን ያፈራች ሀገር መሆኗን ይናገራል።

በአትሌቲክስ ዘርፍ ሀገር ወክሎ መወዳደር እና በግል መወዳደር ልዩነት አለው የሚለው አትሌቱ የሀገርን አርማ አጥልቆና ሰንደቅን ወክሎ መሮጥ ግን የተለየ ኩራትና ክብር አለው ይላል።

በመሆኑም በሁሉም መስክ ለሀገራቸው ሲሉ በጀግንነት መስዋእትነት የከፈሉ ወገኖችን ማክበርና ማመስገን ከሁላችንም የሚጠበቅ ኃላፊነት ነው ብሏል። 

ለሀገር መስዋዕትነት የከፈሉ አያሌ ጀግኖችን ማመስገን፣ ተገቢውን ክብርና ዕውቅና መስጠት ይገባልም ነው ያለው።

በተለያዩ አውደ ውድድሮች አሸናፊ ለመሆን በርካታ ውጣ ውረዶችን ማለፍ ይጠይቃል የሚለው አትሌት ቀነኒሳ ፤ በዚህ ሂደት ውስጥ አልፈው የሀገርን ስም ያስጠሩና ለህዝብ መስዋእትነት የከፈሉ ባለውለታዎችን መዘከርና ማክበር መለመድ አለበት ይላል።

ለሀገርና ለህዝብ የማያልፍ ታሪክ ሰርቶ ማለፍ ትልቅ ክብርና አድናቆት የሚሰጠው መሆኑንም ተናግሯል።

ኢትዮጵያዊያን በሁሉም መሰክ ለሀገር አንድነት፣ አብሮነትና እድገት በጋራ መሮጥ ይጠበቅብናልም ብሏል።

የ2016 አዲስ ዓመት ለሁላችንም የሰላም የፍቅርና የአብሮነት እንዲሁም ለሀገራችን የስኬት ዘመን ይሁን በማለት የመልካም ምኞት መልእክቱን አስተላልፏል።

ጳጉሜን 2 የመሥዋዕትነት ቀን "በመሥዋዕትነት የምትጸና አገር" በሚል መሪ ሀሳብ በመላው ሀገሪቱ በተለያዩ መርሐ-ግብሮች እየተከበረ ይገኛል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም