ቀጥታ፡

ኮሚሽኑ በመጪዎቹ በዓላት የእሳትና ድንገተኛ አደጋዎች እንዳይከሰቱ ህብረተሰቡ ጥንቃቄ እንዲያደርግ አሳሰበ

አዲስ አበባ፤ ጳጉሜን 2/2015(ኢዜአ)፦ በመጪዎቹ በዓላት የእሳትና ድንገተኛ አደጋዎች እንዳይከሰቱ ህብረተሰቡ ጥንቃቄ እንዲያደርግ የእሳትና አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን አሳሰበ።           

 የኮሚሽኑ የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያ አቶ ንጋቱ ማሞ ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ በመጪው አዲስ ዓመትና ቀጥሎ በሚከበሩ በዓላት ሊያጋጥሙ የሚችሉ አደጋዎችን ለመከላከል ዝግጅት ተደርጓል።    

ለዚህም ኮሚሽኑ ከፖሊስ፣ ኤሌክትሪክ ኃይል፣ ውሃና ፍሳሽ እንዲሁም ከትራንስፖርት ተቋማት ጋር ቅንጅት በመፍጠር የጋራ እቅድ መውጣቱን ተናግረዋል።  

ሊከሰቱ የሚችሉ አደጋዎችን ለመቀነስም ኀብረተሰቡ ጥንቃቄ እንዲያደርግ የግንዛቤ ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ገልጸዋል።

በአዲስ ዓመት አከባበር የደመራ እና ችቦ ማብራት ሥነ ሥርዓት ላይ የእሳት አደጋ እንዳይከሰት ሕዝቡ ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባውም አሳስበዋል።      

በመኖሪያ ቤት ውስጥ ችቦ የሚለኩሱ የህብረተሰብ ክፍሎችም ከሶፋ፣ ምንጣፍ፣ ከመጋረጃ ጨርቆችና ሌሎች በቀላሉ ሊቀጣጠሉ ከሚችሉ ቁሶች ጋር ንክኪ እንዳይፈጠር  መጠንቀቅ ተገቢ ነው ብለዋል።

ለአዲስ ዓመትና ለመስቀል ደመራ የሚደመርበት ቦታ ከኤሌክትሪክና የቴሌኮም መስመሮች፣ ከነዳጅ ማደያዎች፣ ከጋራዥ እንዲሁም ከሌሎች የአገልግሎት ተቋማት አቅራቢያ አለመሆኑን ማረጋገጥ አስፈላጊ መሆኑን ተናግረዋል።

በቤት ውስጥ ለምግብ ዝግጅት የሚደረግ የኤሌክትሪክ እና የከሰል አጠቃቀም ላይ እንዲሁም ሻማ በሚለኮስበት ወቅት ሕዝቡ የእሳት አደጋ እንዳይከሰት ጥንቃቄ እንዲያደርግም አሳስበዋል።     

ኮሚሽኑ አደጋዎች እንዳይከሰቱ ከሚያደርገው ጥረት ባሻገር ለሚከሰቱ አደጋዎች ፈጣን ምላሽ ለመስጠት ዝግጅት ማድረጉን ገልጸዋል።

ለዚህም ባለሙያዎች፣ የእሳት ማጥፊያ ተሽከርካሪዎች፣ አምቡላንሶች የ24 ሰዓት አገልግሎት ይሰጣሉ ብለዋል።

ህብረተሰቡም አደጋዎች ብዙ ጉዳት ሳያደርሱ መቆጣጣር እንዲቻል ግልፅና ትክክለኛ በሆነ መንገድ ጥቆማ እንዲያደርግ ጠይቀዋል።  

አቶ ንጋቱ አክለውም የክረምት ወቅት እንደመሆኑ ለጎርፍ እና ሌሎች ልዩ ልዩ አደጋዎች ምላሽ የሚሰጥ ቡድን መዋቀሩን ነው የተናገሩት።   

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም