የሶላር ኢነርጂ ልማት ኢንሼቲቭ የኢትዮጵያን የአገር አቀፍ ኤሌክትሪክ ተደራሽነት ፕሮግራም የሚደግፍ ነው- ዶክተር ኢንጂነር ሱልጣን ወሊ - ኢዜአ አማርኛ
የሶላር ኢነርጂ ልማት ኢንሼቲቭ የኢትዮጵያን የአገር አቀፍ ኤሌክትሪክ ተደራሽነት ፕሮግራም የሚደግፍ ነው- ዶክተር ኢንጂነር ሱልጣን ወሊ
አዲስ አበባ፤ ጳጉሜን 2/2015 (ኢዜአ)፦ በአፍሪካ ልማት ባንክ የሚመራው የሶላር ኢነርጂ ልማት ኢኒሼቲቭ የኢትዮጵያን አገር አቀፍ የኤሌትሪክ ተደራሽነት ፕሮግራም እንደሚያግዝ የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ኢንጂነር ሱልጣን ወሊ ገለጹ።
“በረሃማነትን ወደ ኃይል መለወጥ” በሚል መሪ ሀሳብ የሚተገበረው ኢኒሼቲቭ ኢትዮጵያን ጨምሮ 11 አገሮችን የሚያካትት ነው።
በኢኒሼቲቩ አማካኝነት እስከ 10 ሺህ ሜጋ ዋት የሚደርስ የሶላር ኢነርጂ እንደሚለማ ተመላክቷል።
ላለፉት ሶስት ቀናት በናይሮቢ ኬንያ ሲካሄድ የቆየው የአፍሪካ የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ ተካሂዷል።
የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የኢነርጂ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ኢንጂነር ሱልጣን ወሊ ከጉባኤው ጎን ለጎን በአፍሪካ ያለውን ግዙፍ የታዳሽ ኢነርጂ ሀብት የግሉን ዘርፍ በማሳተፍ ማልማት በሚቻልበትና የዜጎችን የኢነርጂ ተደራሽነትን በማስፋት አገራዊ ኢኮኖሚን ማሳደግ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ በተዘጋጀው የሚኒስትሮች ስብሰባ ላይ ተሳትፈዋል።
ሚኒስትር ዴኤታው በስብሰባው ላይ ባደረጉት ገለጻ የታዳሽ ኢነርጂ ተደራሽነትን ማሳደግ ለአንድ አገር ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ከሚያደርገው አስተዋፅኦ በተጨማሪ የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋምና ለመታደግ ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንደሚያበረክት አመልክተዋል።
ምንም እንኳ ኢትዮጵያ ያላት የታዳሽ ኢነርጂ ሃብት ከፍተኛ ቢሆንም እስከ አሁን ሊለማ የቻለው ከ5 ነጥብ 4 ጊጋ ዋት እንደማይበልጥና የኤሌክትሪክ ተደራሽነት ከ51 በመቶ በታች እንደሆነ አንስተዋል።
የኢነርጂ ልማትና ተደራሽነትን ለማሳደግ የግሉ ዘርፍ ተሳትፎ ወሳኝ በመሆኑ ኢትዮጵያ የኢነርጂና ኢንቨስትመንት ፖሊሲዎቿን በማሻሻል፣ የመንግሥትና የግል አጋርነት ህግ አውጥታ እየተገበረች መሆኗን ገልጸዋል።
በቅርቡ በአፍሪካ ልማት ባንክ መሪነት የተጀመረው የሶላር ኢነርጂ ልማት ኢኒሼቲቭ ኢትዮጵያ ለምታደርገው የአገር አቀፍ ኤሌክትሪክ ተደራሽነት ኘሮግራም አጋዥ እንደሚሆን አመልክተዋል።
ኢኒሼቲቩ በታቀደለት ጊዜ በፍጥነት ወደ ስራ እንዲገባ ሚኒስትር ዴኤታው ጥሪ ማቅረባቸውን ከውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
በጉባኤው ላይ የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ፣ የግብርና ሚኒስቴር ሚኒስትር ዶክተር ግርማ አመንቴ፤ የአገራት መሪዎች፣ ሚኒስትሮችን ጨምሮ ከ10ሺ በላይ የተለያዩ የዘርፋ ተዋናይ የሆኑ ግለሰቦች ተገኝተዋል፡፡