ሀገር ጸንታ የቆየችው በጀግኖቿ በተከፈለ መሥዋእትነት ነው - ተመላሽ የመከላከያ ሠራዊት አባላት - ኢዜአ አማርኛ
ሀገር ጸንታ የቆየችው በጀግኖቿ በተከፈለ መሥዋእትነት ነው - ተመላሽ የመከላከያ ሠራዊት አባላት
ሚዛን አማን ፤ ጳጉሜን 2/2015 (ኢዜአ)፦ ሀገር ጸንታ የቆየችው በጀግኖቿ በተከፈለ መሥዋእትነት ነው ሲሉ በሚዛን አማን ከተማ የሚኖሩ ተመላሽ የመከላከያ ሠራዊት አባላት ገለጹ።
ጳጉሜን 2 የመሥዋእትነት ቀን "በመሥዋእትነት የምትጸና ሀገር" በሚል መሪ ሀሳብ ዛሬ በሀገር አቀፍ ደረጃ እየተከበረ ሲሆን ተመላሽ የመከላከያ ሰራዊት አባላት እለቱን ምክንያት በማድረግ ለኢዜአ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
በአስተያየታቸውም በትውልድ ቅብብሎሽ ውስጥ በየጊዜው የህይወት መሥዋዕትነት እየተከፈለላት ለዛሬ የበቃች ኢትዮጵያን ከነክብሯ ለማስቀጠል ዋጋ የሚከፍለውን የመከላከያ ሰራዊትን ማሰብና ማክበር ተገቢ ነው።
በእለቱ ለኢትዮጵያ ልዕልና በየጊዜው ዋጋ እየከፈለ ያለውን የመከላከያ ሠራዊት ማሰብና ተገቢውን ክብር መስጠት ያስፈልጋል ሲሉም አክለዋል።
የሚዛን አማን ከተማ ነዋሪ የሆኑት ተመላሽ የመከላከያ ሠራዊት አባል ሃምሳ አለቃ ጴጥሮስ ባንዝኬዝ እንዳሉት ሀገር ዋጋ ሳይከፈልላት ሉአላዊነቷ ሊከበር አይችልም።
ለአሥራ ሁለት ዓመታት የመከላከያ ሠራዊት አባል ሆነው ኢትዮጵያን ለመውረር ከሚፋለሙ ጠላቶች ጋር ሲዋጉ እጃቸው ላይ በጥይት መመታታቸውን አስታውሰው ለሀገር የተከፈለ ዋጋ በመሆኑ ወደ ኋላ ሳይሉ ትግላቸውን መቀጠላቸውን ገልጸዋል።
"ወታደር ከሀገርና የህዝብ ሰላም ያለፈ የኔ የሚለው ነገር የለውም" ያሉት ሃምሳ አለቃ ጴጥሮስ "በሀገር ፍቅር ስሜት በመመራት ደሙን አፍስሶ አጥንቱን ከስክሶ ዜጎች በክብር እንዲቆሙ የሚያደርግ ነው" ብለዋል።
ለሀገሩ ሲል ረሃብና ጥምን ከበረሃ ሀሩር ጋር በመጋፈጥ ራሱን መሥዋዕት አድርጎ በማቅረብ ሀገር ለሚያጸና ወታደር ክብርና እውቅና መስጠት ተገቢ መሆኑን ተናግረዋል።
"ዛሬም ለሀገር ሉአላዊነት መከበርና ለዜጎች ደህንነት መጠበቅ መሥዋዕትነት እየከፈለ ላለው መከላከያ ሠራዊት ተገቢውን ክብር መስጠት ከኢትዮጵያውያን የሚጠበቅ ነው" ሲሉም አመልክተዋል።
ሌላው የከተማዋ ነዋሪ ተመላሽ የመከላከያ ሠራዊት አባል አሥር አለቃ ከተማ ዘለቀ በበኩላቸው "መከላከያ ሰራዊት የሀገር ፍቅርን ብቻ በልቡ ሰንቆ በጀግንነት እስከ ሞት የሚታገል የኢትዮጵያ አለኝታ ነው" ብለዋል።
ወታደር ሀገርን ከእነ ክብሯና ዳር ድንበሯ ለትውልድ ለማስተላለፍ ለህይወቱ የማይሰስት የሀገር አለኝታ እንደሆነ ተናግረዋል።
ወታደር በጥይት ተመትቶም ቢሆን ለውጊያ ከመሰለፍ ወደ ኋላ የማይል ወኔ ያለው የሀገር መከታ መሆኑን ገልጸዋል።
"ጠላት ሀገራችንን ከሚወር ሞት ይሻለኛል በሚል ወኔ እንደ ሻማ ራሱ ቀልጦ ለሀገር የነጻነት ብርሃን እየሆነ ያለውን መከላከያ ሠራዊት ማሰብና ማበረታታት ከዜጎች የሚጠቅ ነው" ብለዋል።
ለሀገሩ ሲል ዋጋ እየከፈለ ያለውን ወታደር "ለኔ ሲል ነው" የሚል ትውልድ መፍጠር እንደሚገባም አስገንዝበዋል።
"ትላንት አባቶቻችን የከፈሉት የህይወት እንዲሁም የደምና አጥንት መሥዋዕትነት ኢትዮጵያን ለዛሬ ከነክብሯ እንዳደረሰ ለነገይቱ ሉዓላዊት ኢትዮጵያ ደግሞ የሀገር መከላከያ ሠራዊት ተመሳሳይ መሥዋዕትነት እየከፈለ ይገኛል፤ ክብር ይገባዋል" ሲሉ መልእክት አስተላልፈዋል።