ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ ክብሯን ጠብቃ በፅናት የቆመችው በህዝቧና በጀግኖች የፀጥታ ኃይሎች መስዋዕትነት ነው-የቀድሞ ሠራዊት አመራሮች

አዲስ አበባ ፤ ጳጉሜን 2/2015 (ኢዜአ) ፦ የኢትዮጵያ ሉዓላዊ የግዛት አንድነቷንና ክብሯን አስጠብቃ በፅናት የቆመችው በህዝቧና የፀጥታ ኃይሎች በከፈሉት መስዋዕትነት መሆኑን የቀድሞ የኢትዮጵያ ሠራዊት ከፍተኛ አመራሮች ተናገሩ።

መከላከያ ሰራዊትና ሌሎች የፀጥታ ኃይሎች ለህዝብ ሰላምና ለሀገር አንድነት ለሚከፍሉት ዋጋ ምስጋና እንደሚገባም ነው የገለጹት።

ኢትዮጵያ የሺህ ዓመታት ገናና ስልጣኔ ባለቤት፣ በየትኛውም ኃይል ያልተደፈረ ሉዓላዊ የግዛት አንድነትና ቅኝ ያልተገዛች ብቸኛዋ አፍሪካዊት ሀገር በመሆን ደማቅ ታሪኳ በዓለም መዛግብት ሰፍሯል።

በቀድሞው ሰራዊት ወደር የሌለው የኢትዮጵያ የጦር ሜዳ ጀግና ሜዳይ ተሸላሚ ብርጋዴር ጄነራል ተስፋዬ ሃብተማርያም፤ ኢትዮጵያ በረጅሙ ታሪኳ በርካታ የውስጥና የውጭ ጠላቶች ቢያጋጥሟትም ሁሉንም በማሸነፍ በፅናት ቀጥላለች።

ሀገር በፅናት እንድትቆምና ያጋጠሟትን ፈተናዎች አልፋ በክብር እንድትቀጥል ከቅድመ አያቶቻችን ጀምሮ ኢትዮጵያውያን የህይወት ዋጋ ከፍለዋል ነው ያሉት።

አሁን ያለው የሀገር መከላከያ ሰራዊትም የኢትዮጵያውያን ክብርና ሉዓላዊነት ለማስቀጠል የጀግንነት ታሪክ በመጸፈም ላይ ይገኛል ብለዋል።

ሌላኛው የቀድሞ የኢትዮጵያ ሠራዊት አመራር ሻለቃ ታመነ አባተ፤ ኢትዮጵያ በየዘመኑ ለክብሯ የሚዋደቁ ጀግኖች ልጆች እንዳሏት አሳይታለች ብለዋል።

የህዝብ አንድነት፣ የሀገር ፍቅር እንዲሁም የፀጥታ ኃይሎቿ በሉዓላዊነት የማይደራደሩ መሆን ኢትዮጵያ በፅናትና በክብር የቆየች ሀገር እንድትሆን ትልቅ ሚና መጫወቱን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያውያን በየዘመናቸው ለሀገር ተጋድሎ ማድረጋቸውን ያነሱት ሃምሳ አለቃ ብርሃኑ አማረ፤ ህዝቡ ለሀገሩ ያለው ቀናኢነት ወደር የለሽ እንደሆነ ጠቅሰዋል።

በአሁኑ ወቅትም ሠራዊቱ በእውቀት፣ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ፣ በፅናትና በጀግንነት የሀገርን ዳር ድንበር እያስከበረ መሆኑን አብራርተዋል።

የቀድሞ የኢትዮጵያ ጦር ሰራዊት አመራሮች አክለውም ሀገር በፅናት እንድትቀጥል መስዋዕትነት እየከፈሉ ያሉ ጀግኖች ተገቢውን ክብር እንዲያገኙ ማድረግ እንደሚገባ ተናግረዋል።

የህይወት መስዋዕትነት በምንም የማይተካና ለሀገር የሚከፈል ወደር የለሽ የጀግንነት ስራ መሆኑን በአግባቡ መገንዘብ እንዳለበትም ጠቅሰዋል።

ጀግኖችን ማመስገን  ሌሎች ሀገር ተረካቢ ጀግኖችን ለማፍራት ትልቅ ሚና አለው ያሉት የቀድሞ ወታደራዊ መኮንኖቹ፤ ታሪካቸውን በወርቅ ቀለም መጻፍና ትውልድ እንዲማርበት መስራት አስፈላጊ ነው ብለዋል።

ኢትዮጵያ በመጪዎቹ ዘመናትም ጠንካራና ለጠላቶቿ የማትበገር ሀገር ሆና እንድትቀጥል ትውልዱ በቀደምት አትዮጵያውያን ጀግኖች ስነልቦና መቅረፅ አስፈላጊ መሆኑን ጠቅሰዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም