ቀጥታ፡

የመንግስት አገልግሎትና አስተዳደር ስርዓት ማሻሻያ ሪፎርም በተመረጡ ተቋማት ተግባራዊ ይደረጋል-ዶክተር መኩሪያ ኃይሌ

አዲስ አበባ ፤ ጳጉሜን 1/2015 (ኢዜአ) ፡- በተያዘው በጀት ዓመት የመንግስት አገልግሎትና አስተዳደር ስርዓት ማሻሻያ ሪፎርም በተመረጡ ተቋማት ተግባራዊ እንደሚደረግ የሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽነር ዶክተር መኩሪያ ኃይሌ ተናገሩ፡፡

ሪፎርሙ በተለይ የመንግስት አገልግሎት አሰጣጥን በማሻሻል በኩል የተሻለ ለውጥ እንደሚያመጣ ነው የተናገሩት፡፡

ዶክተር መኩሪያ ኃይሌ ይህን ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ አገራቸውን ከ38 ዓመታት በላይ ላገለገሉ ሰራተኞች እውቅና በሰጡበት ውቅት ባደረጉት ንግግር ነው፡፡

በንግግራቸውም ብቁና አገራቸውን በታማኝነት የሚያገለግሉ ዜጎች ለኢትዮጵያ እድገት ወሳኝ ሚና እንደሚጫወቱ ገልጸዋል፡፡

በተለይ የመንግስት ተቋማት አሰራራቸውን በማዘመን ቀልጣፋ አገልግሎት ተደራሽ ማድረግ እንደሚጠበቅባቸው ነው የጠቆሙት፡፡

ከዚህ አኳያ የመንግስት አገልግሎትና አስተዳደር ስርዓት ማሻሻያ ሪፎርም መዘጋጀቱን ጠቅሰው፤ ለሪፎርሙ ማስፈጸሚያ የሚሆኑ የፖሊሲ ሰነድና ስትራቴጂዎች እንዲሁም የህግ ማእቀፎች በመጠናቀቅ ላይ ናቸው ብለዋል፡፡

ሪፎርሙ በኢትዮጵያ የመንግስት አገልግሎት አሰጣጥ በማዘመንና በማቀላጠፍ በኩል መሰረታዊ ለውጥ እንደሚያመጣም ነው ያብራሩት፡፡

የሪፎርሙ የዝግጅት ስራ በበጀት ዓመቱ የመጀመሪያ ስድስት ወራት ውስጥ እንደሚጠናቀቅም ጠቁመዋል፡፡

ይህን ተከትሎም በሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን፣ በጤና ሚኒስቴር፣ በትምህርት ሚኒስቴር፣ በግብርና ሚኒስቴር፣ በፕላንና ልማት ሚኒስቴርና በገንዘብ ሚኒስቴር የሪፎርሙ ሙከራ ትግበራ ይካሄዳል ነው ያሉት፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም