የአገልጋይነት ቀን በጅቡቲ ሸበሌ መርከብ ላይ በተለያዩ መርሃ ግብሮች ተከበረ - ኢዜአ አማርኛ
የአገልጋይነት ቀን በጅቡቲ ሸበሌ መርከብ ላይ በተለያዩ መርሃ ግብሮች ተከበረ
አዲስ አበባ ፤ ጳጉሜን 1/2015 (ኢዜአ)፦ የአገልጋይነት ቀን በጅቡቲ ሸበሌ መርከብ ላይ እውቅናና ምስጋና በመስጠት መከበሩን የኢትዮጵያ የባሕር ትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ አስታወቀ።
የአገልጋይነት ቀን ከሀገር ርቀው ሀገራቸውን በትጋት እያገለገሉ ካሉ ባሕረተኞች፣ የከባድ መኪና አሽከርካሪዎችና የወጪ ገቢ ንግዱን በማቀላጠፍ በኩል ድርሻ ካላቸው በጅቡቲ የቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ሰራተኞችና የትራንዚት እና ጉምሩክ ሠራተኞች በጅቡቱ ዶራሌ ሁለገብ ወደብ በሸበሌ መርከብ ላይ ተከብሯል፡፡
በመርሃ ግብሩ ላይ በጅቡቲ የኢትዮጵያ ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ብርሃኑ ፀጋዬ፣ የዶራሌ ሁለገብ ወደብ ዋና ስራ አስፈፃሚ ጃማ ኢብራሂም ዳራር፣ በኢባትሎ የሺፒንግ አገልግሎት ዘርፍ ምክትል ዋና ስራ አስፈፃሚ ካፒቴን ወንደሰን ካሳ፣ በኢባትሎ የጅቡቲ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ስራ አስኪያጅ አቶ ታዬ ጫላ እና የሸበሌ መርከብ አዛዥ ካፕቴን ደረጄ ዕለቱን በማስመልከት መልዕክት ማስተላለፋቸው ተገልጿል፡፡
በመርሃ ግብሩ በረዥሙ የሎጅስቲክስ ሰንሰለት የሀገራችንን የወጪ ገቢ ንግድ በባሕር እና በየብስ በማጓጓዝ በተፈለገው ጊዜ እና በተፈለገው ቦታ ለማድረስ ቀን እና ሌሊት ሀገራችሁን በትጋት ላገለገሉ አካላት ተመስግነዋል።
ለታታሪ አገልጋዮች የተዘጋጀውን የምስጋና እና የዕውቅና የምስክር ወረቀት አምባሳደር ብርሃኑ ፀጋዬ ማበርከታቸውም ተገልጿል፡፡