ስናገለግል የሀገራችንን ብሩሀ ተስፋ እያሰብን ይሁን--ዶክተር ለገሰ ቱሉ - ኢዜአ አማርኛ
ስናገለግል የሀገራችንን ብሩሀ ተስፋ እያሰብን ይሁን--ዶክተር ለገሰ ቱሉ
አዲስ አበባ ፤ ጳጉሜን 1/2015 (ኢዜአ)፦ “ስናገለግል የሀገራችንን ብሩሀ ተስፋ እያሰብን ይሁን ሲሉ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዶክተር ለገሰ ቱሉ ገለጹ፡፡
ጳጉሜን 1 የአገልጋይነት ቀን "ኢትዮጵያን እናገልግል" በሚል መሪ ሃሳብ በመላ ሀገሪቱ እየተከበረ ነው፡፡
ዶክተር ለገሰ ቱሉ የአገልጋይነት ቀንን አስመልክተው በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት ማገልገል ክብር ነው፤ እንደ ኢትዮጵያ በብዙ ተስፋና ፈተና ያለች ሀገርን ማገልገል ደግሞ ድርብ ክብር ነው ሲሉም ገልጸዋል፡፡
“በመላው ሀገራችን የዛሬውን ቀን ስናከብር ለሀገራችን በየተሰማራንበት ዘርፍ ውጤታማ የሆነ አገልግሎት በመስጠት የራሳችንን ዐሻራ እያሳረፍን መሆናችንን በማመን ሊሆን ይገባል” ሲሉም አስገንዝበዋል፡፡
ኢትዮጵያ ከ2 ነጥብ 4 ሚሊዮን በላይ የመንግስት ሰራተኞች አሏት፤ ይህ ቁጥር ቀላል የማይባሉ ሀገራት የህዝብ ቁጥር ነው ብለዋል፡፡
የአገልግሎት አሰጣጣችንን በማሻሻል በቁጥራችን ልክ የሚገባንን ኃላፊነት ከተወጣን በብዙ መልኩ ለነገው ትውልድ መንገድ በመጥረግ ጉልህ ዐሻራችንን እያስቀምጥን መሆኑን ልንጠራጠር አይገባም ሲሉም ገልጸዋል፡፡
የኢትዮጵያ ልማት እና ቀጣይ እድገት ብሎም የሰላም መሰረት አገልገሎት አሰጣጣችን ያለው ሚና በቀላሉ የሚታይ አይደለም ሲሉም አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡
የኢኮኖሚ እድገቱን ቀጣይነት ለማረጋገጥ ፈጣን የሆነ አገልግሎት መስጠት የግድ መሆኑን ለአፍታም ቢሆን ልንርሳው የማይገባ ጉዳይ ነው ያሉት ሚኒስትሩ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በብዙ ውስጣዊ እና ዓለም አቀፋዊ ፈተናዎች እየተፈተነ በዓለም በፈጣን እድገት ላይ ካሉ ሀገራት ተርታ የሚመደብ ነው ብለዋል፡፡
በሀገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያ የተመዘገቡ አበረታች ውጤቶች በቀጣይ ሙሉ ፍሬ እንዲያፈሩ የአገልገሎት አሰጣጥ ማሻሻያዎች እና የሲቪል ሰርቪስ ማሻሻያዎች ተግባራት በመንግስት በኩል እየተከናወኑ እንደሚገኙ ጠቅሰዋል፡፡
እነዚህ ጅምር የለውጥ ተግባራት በሙሉ ፍሬ ለሕዝቡ ደርሰው በዘላቂነት ችግሩ እንዲፈታ እኔ በተሰማራሁበት መስክ፣ በያዝኩት የስራ መደብ የሚጠበቅብኝን ሃላፊነት እየተወጣሁ መሆን እና አለመሆኑን መጠየቅ ከሁላችንም የሚጠበቅ ኃላፊነት መሆኑን ገልጸዋል፡፡
“በትብብር እና በጋራ መንፈስ ችግራችንን እየፈታን፣ አገልገሎት አሰጣጣችንን እያዘመን ወደ ፊት ከተራመድን የበለጸገች ኢትዮጵያን እውን ማድረጋችን አይቀሬ ነው” ብለዋል፡፡