ምስጉንና ትጉህ የጤና ባለሙያ አርጃ ቲሎ

 የጤና መኮንን ባለሙያው  አርጃ ቲሎ በጂንካ አጠቃላይ ሆስፒታል ምስጉን እና ታታሪ ሠራተኛ ናቸው።

በጂንካ አጠቃላይ ሆስፒታል የተቀናጀ ድንገተኛ የማህፀን ፅንስና አጠቃላይ ቀዶ ህክምና ባለሙያው ከ35 ዓመታት በላይ በተለያዩ ተቋማትና አካባቢዎች ሀገራቸውን አገልግለዋል።

ካገለገሉባቸውም አካባቢዎች በጋሞ፣ወላይታና ደቡብ ኦሞ ዞኖችን ጨምሮ ሀዋሳና ጂንካ ተጠቃሽ ናቸው።

የህክምና ትምህርታቸውን በሀገር ውሰጥና በውጭ ሃገር በመከታተል ሙያቸውን  አሻሽለዋል።

 የጤና መኮንን ባለሙያው አርጃ ቲሎ በበዓላትና በእረፍት ቀናት ጭምር ከቤተሰብ ይልቅ ለታካሚዎቻቸው ቅድሚያ በመስጠታቸው ምስጋናን ተችረዋል ።


ከሌሎች ሰራተኞች ከመግባታቸው በፊት ቀድመው ቢሮ መግባታቸውና ታታሪነታቸው ለሽልማት አብቅተቸዋል፡፡ 

ባለሙያው አርጃ ቲሎ ባለፈው አመት ከደቡብ ኦሞ ዞን ፐብሊክ ሰርቪስ እና የሰው ሀብት ልማት መምሪያ የዋንጫና የወርቅ ሜዳሊያ ሽልማትን ተቀብለዋል።

በ35 ዓመታት የስራ ቆይታቸው ብዙ ነገሮችን ያሳለፉት ባለሙያው አርጃ ቲሎ ታዲያ አንዴ ያጋጠማቸውን ከባድ ፈተና መቼም እንደማይረሱት ይናገራሉ ።

በጂንካ ሆስፒታል በማገልገል ላይ እያሉ አንዲት ነፍሰ ጡር እናት በወሊድ ወቅት ባጋጠማት የተራዘመ ምጥ በሞትና በህይወት መካከል ነበረች ሲሉ ያስታውሳሉ።

ይቀጥሉናም በወቅቱ በሆስፒታሉ የደም አቅርቦት እና በዘርፉ የሰለጠኑ ስፔሻሊስት ሀኪሞች ባለመኖራቸው ለዚህች እናት ህክምና መስጠት አልተቻለም ነበር  ።


 

ስፔሻሊስቱ ለተሻለ ህክምና ወደ አርባ ምንጭ ሆስፒታል ሪፈር መፃፍ ቢጠበቅባቸውም ታካሚዋ እስከ አርባ ምንጭ በህይወት ስለመድረሷ ይጠራጠራሉ ሲሉ ትውስታቸውን ይተርካሉ።

ይህን የተገነዘቡት የጤና መኮንኑ ታዲያ አንድ ነገር ለማድረግ ወሰኑ፡፡  ወደ አርባ ምንጭ ልከው ነፍሰ ጡሯ መንገድ ላይ ህይወቷ ከሚያልፍ አቅማቸው የፈቀደውን አድርገው የመጣውን ለመቀበል ወሰኑ።

ውሳኔውም ህክምናውን ሳያደርጉ ሞቷን ከመጠባበቅ እንደሚሻል በማመን ከህመምተኛዋ ቤተሰቦች ባገኙት ደም የተሳካ የቀዶ ጥገና በማድረግ ወላዷን እናት ከሞት ሊታደጉ መቻላቸውን በኩራት ይተርካሉ።

'የፈጣሪ እርዳታ ታክሎበት ቀዶ ጥገናውን በተሳካ ሁኔታ አጠናቅቄያለሁ' ታካሚዋም በህይወት ቆይታ ጤናማ ህይወት ስትመራ በማየታቸው ቃላት ሊገልፁት የማይችሉት ደስታ ይሰማቸዋል።

በመሆኑም ማንኛውም ሀኪም ቁሳቁስ አልተሟላም እጥረት አለ በማለት ከማማረርና ባለው አቅም ተገልጋዩን በማገልገል ኃላፊነቱን ይወጣ ሲሉም  ምክራቸውን ይለግሳሉ።

የረጅም አመታት የስራ ባልደረባ አቶ ኢያሱ ታንቱ የአርጃን ከሰራተኛው ጋር ተግባቢነት ፣ደከመኝ ሰለቸኝ የማያውቁ፣ለስራቸውና ለስራ ባልደረቦቻቸው ክብር ያላቸው ፣ታካሚውን በርህራሄ የሚያገለግሉ፣ ለሌሎች ተምሳሌት የሚሆኑ ሲሉም ይገልጿቸዋል።

በጅንካ አጠቃላይ ሆስፒታል በቀዶ ህክምና ክፍል የነርሶች አስተባባሪ አቶ አማኑኤል ካሳ የባልደረባቸውነ ምስክርነት ይጋራሉ።

የሆስፒታሉ ሜዲካል ዳይሬክተር ዶክተር አይፎክሩ ግዛቸው በበኩላቸው አቶ አርጄ በሆስፒታሉ ስፔሻሊስት ሀኪሞች ከመመደባቸው አስቀድሞ ስፔሻሊስት ሀኪሞች እጥረት በነበረበት ወቅት በአጠቃላይ ቀዶ ህክምናና ነፍሰ ጡር  እናቶችን በቀዶ ህክምና በማዋለድ ትልቅ ሙያዊ ኃላፊነት ሲወጡ የነበሩ ትጉህ ሰራተኛና የሀገር ባለውለታ ናቸው ሲሉ ይመሰክራሉ።

ወይዘሮ ዘላለም ሰኢድ የጅንካ ከተማ ነዋሪ ናቸው፤ የአርጃ ቲሎ የህክምና ሙያ ከጎበኟቸው ተገልጋዮች አንዷ ሲሆኑ የሀኪሙን መልካምነት ይመሰክራሉ፡፡ እንዲ ሲሉ የህክምና ሙያን ከመልካም ስነምግባር ጋር የያዙ።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም