ኢትዮጵያን ማገልገል ድርብ ክብር በመሆኑ ደከመኝ ሰለቸኝ ሳንል እናገልግል-ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያን ማገልገል ድርብ ክብር በመሆኑ ደከመኝ ሰለቸኝ ሳንል እናገልግል-ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ

አዲስ አበባ ፤ ጳጉሜን 1/2015 (ኢዜአ) ፦ ኢትዮጵያን ማገልገል ድርብ ክብር በመሆኑ ደከመኝ ሰለቸኝ ሳንል እናገልግል ሲሉ የሴቶች እና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ ተናገሩ።
የሴቶች እና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ በአስኮ መናኸሪያ የአገልጋይነት ቀንን አስጀምረዋል።
ሚኒስትሯ በዚሁ ወቅት እንዳሉት እለቱ በመጪው ዓመት ለህብረተሰቡ የላቀ አገልግሎት ለመስጠት ቃል የሚገባበት ነው ብለዋል።
የትራንስፖርት እና ሎጅስቲክ ዘርፍ ለሀገር ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑን ገልጸው ፤ ለዘርፉ ተዋናዮች ምስጋና አቅርበዋል።
የዘርፉ አንቀሳቃሾች የኢትዮጵያን ገጽታ ከፍ በማድረግ ማህበራዊ ትስስርን በማጠናከር ረገድ ላከናወኑት ስራ ኢትዮጵያ ታመሰግናችኋለች ብለዋል።
ኢትዮጵያን ማገልገል ድርብ ክብር መሆኑንም ገልጸው፤ ኢትዮጵያን ደከመኝ ሰለቸኝ ሳንል እናገልግላት ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
በቀጣይም የዘርፉን አገልግሎት አሰጣጥ በማሻሻል የትራፊክ አደጋን በጋራ መግታት እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
የፌደሬሽን ምክር ቤት ምክትል አፈ-ጉባኤ ዘሀራ ዑመድ በበኩላቸው ሁሉም በተሰማረበት ህዝቡን በቅንነትና በታማኝነት ማገልገል ክብር መሆኑን ገልጸዋል።
ሁሉም በተሰማራበት የሚያበረክተው በጎ አገልግሎት፤ ኢትዮጵያ ከፍ የሚያደርግና የዜጎችን አንድነትና ህብረት የሚያጠናክር የተከበረ ድርጊት መሆኑን አንስተዋል።
የትራንስፖርት ዘርፉ ተዋንያንም የተሰጣቸውን ትልቅ አደራ በጥንቃቄ በማሽከርከርና ዜጎችን በቅንነት በማገልገል ሃላፊነታቸውን ሊወጡ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
የትራንስፖርት እና ሎጅስቲክ ሚኒስትር ዴኤታ ደንጌ ቦሩ በበኩላቸው ዝቅ ብሎ ማገልገል ከፍታን የሚያስገኝ ነው ብለዋል።
ኢትዮጵያ ከማገልገል በላይ ትልቅ ክብር እንደሌለ ገልጸው፤ ሁሉም በተሰማራበት መስክ ሀገሩን በታማኝነት ሊያገለግል እንደሚገባ አመላክተዋል።