ኤጀንሲው ዘመናዊ ቴክኖሎጂ በመጠቀም ቀልጣፋ እና ተገቢውን አገልግሎት ለህብረተሰቡ ሊሰጥ ይገባል-ከንቲባ አዳነች አቤቤ - ኢዜአ አማርኛ
ኤጀንሲው ዘመናዊ ቴክኖሎጂ በመጠቀም ቀልጣፋ እና ተገቢውን አገልግሎት ለህብረተሰቡ ሊሰጥ ይገባል-ከንቲባ አዳነች አቤቤ
አዲስ አበባ ፤ ጳጉሜን 1/2015 (ኢዜአ) ፦ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሲቪል ምዝገባና የነዋሪዎች አገልግሎት ኤጀንሲ ያለውን ዘመናዊ ቴክኖሎጂ በመጠቀም ቀልጣፋ እና ተገቢውን አገልግሎት ለህብረተሰቡ ሊሰጥ እንደሚገባ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለፁ።
ከንቲባ አዳነች አቤቤ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የተደረጃውን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሲቪል ምዝገባና የነዋሪነት አገልግሎት ኤጀንሲ ዋና መስርያ ቤት መርቀው ለአገልግሎት ክፍት አድርገዋል።
በዋና መስርያ ቤት ምረቃ መርሃግብር ላይ ከንቲባ አዳነች አቤቤን ጨምሮ ከፍተኛ የመንግሥት የስራ ሃላፊዎች እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተግኝተዋል።
ከንቲባ አዳነች አቤቤ በዚህ ወቅት እንዳሉት፤ ኤጀንሲው ያለውን ዘመናዊ ቴክኖሎጂ በመጠቀም ቀልጣፋ እና ተገቢውን አገልግሎት ለህብረተሰቡ ሊሰጥ እንደሚገባ ገልፀዋል ።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሲቪል ምዝገባ እና የነዋሪነት አገልግሎት ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ ዮናስ ዓለማየሁ በበኩላቸው ተቋሙ ዘመናዊ አገልግሎትን መስጠት የሚያስችለውን የዋና መስሪያ ቤት እድሳት አጠናቆ ለምረቃ አብቅቷል ብለዋል።
ኤጀንሲው እስካሁን ከ1 ሚሊየን በላይ ለሚሆኑ የከተማው ነዋሪዎች የዲጂታል መታወቂያ ተጠቃሚ ማድረጉን ነው የገለፁት።
ይሁን እንጂ ኤጀንሲው ለከተማዋ ነዋሪዎች የሚሰጠውን አገልግሎት ለማዘመን ዘርፈ ብዙ ስራዎችን ቢሰራም ህብረተሰቡ ካለው ፍላጎት አንፃር ብዙ የቤት ስራ ይጠበቅበታል ብለዋል።
በተመሳሳይ በመዲናዋ በሚገኙ ዘጠኝ ክፍለ ከተሞች የሚገኙ ከ30 በላይ የኤጀንሲው ፅህፈት ቤቶች እንደሚመረቁ ከተቋሙ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል ።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ጳጉሜ 1 የአገልጋይነት ቀን ፣ ጳጉሜ 2 የመስዋዕትነት ቀን፣ ጳጉሜን 3 የበጎነት ቀን፣ ጳጉሜ 4 የአምራችነት ቀን ፣ ጳጉሜ 5 የትውልድ ቀን ፣ ጳጉሜ 6 የአብሮነት ቀን የሚል ስያሜ እንደሰጣቸውና በእያንዳንዱ ስድስት ቀናቶች ልዩ ልዩ መርሀ ግብሮች እንደሚከናወኑ መግለፁ ይታወሳል።