በአገልግሎት አሰጣጥ የሚስዋሉ ችግሮችን ለመፍታት የአገልጋይነት ባህልን ለማዳበር መስራት ይገባል - ዶክተር ኢንጅነር ነጋሽ ዋጌሾ - ኢዜአ አማርኛ
በአገልግሎት አሰጣጥ የሚስዋሉ ችግሮችን ለመፍታት የአገልጋይነት ባህልን ለማዳበር መስራት ይገባል - ዶክተር ኢንጅነር ነጋሽ ዋጌሾ
ቦንጋ፣ ጳጉሜ 1 / 2015 (ኢዜአ):- በአገልግሎት አሰጣጥ ዙሪያ የሚስዋሉ ችግሮችን ለመፍታት የአገልጋይነት ባህልን ለማዳበር መስራት ይጠበቅብናል ሲሉ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳደር ዶክተር ኢንጅነር ነጋሽ ዋጌሾ አስገነዘቡ።
ጳጉሜ አንድ የ"አገልጋይነት ቀን"ን አስመልክቶ የክልሉ አመራሮችና ሰራተኞች "አገልጋይነት ክብር ነው" በሚል መሪ ሀሳብ በቦንጋ ከተማ የምክክር መድረክ አካሂደዋል።
አገልጋይነት ክብር በመሆኑ እውቅና ለመስጠት ታስቦ ከስድስቱ የጶጉሜ ቀናቶች የመጀመሪያውን ቀን በሀገር አቀፍ ደረጃ የአገልጋይነት ቀን በመባል ተሰይሟል።
በመድረኩ ላይ የተገኙት የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ፣ በአገልግሎት አሰጣጥ ዙሪያ የሚስተዋሉ ችግሮችና ቅሬታዎችን ለመፍታት የአገልጋይነት ባህልን ማዳበር ያስፈልጋል ።
ፕብሊክ ሰርቪሱ ትልቁን የመንግስትና የህዝብ ሀላፊነት የተሸከመ ሀይል መሆኑን አንስተው "ያለብንን ትልቅ ሃላፊነት በመረዳትና ስንቀጠር በገባነው ቃል መሰረት ህዝብን በአገልጋይነት ስሜት የማገልገል ባህል ማጎልበት ይገባናል። ብለዋል።።
ሀገራቱ ጠንካራ የመፈፀምና የማስፈፀም አቅም ያለው የሰው ሀይል መገንባት በመቻላቸው ለህዝቡ የሚሰጡት አገልግሎች ቀልጣፋና ከቅሬታ የፀዳ መሆኑንም አንስተዋል።
በክልሉ አገልግሎት አሰጣጥን ለማሻሻል ትኩረት ተሰጥቶት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
የመንግስት ሰራተኛውን መብትና ጥቅማጥቅም ከማስከበር አንፃር የክልሉ መንግስት ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሰራም አረጋግጠዋል።
በሲቪል ሰርቫንቱ ዘንድ ለሀገርና ህዝብ የመወገን ጠንካራ እሳቤ መኖሩ ለቀጣይ አገልግሎት አሰጣጥን ለማሻሻል ጥሩ ስንቅ መሆኑንም ዶክተር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ ገልፀዋል።
"በአንዳንድ ተቋማት ሰራተኞች ዘንድ እየተስተዋለ ያለው እጅ መንሻ መቀበል፣ የስራ ሰዓት ያለማክበርና ከውጤታማነት ጋር ተያይዞ ያሉ ክፍተቶች በቀጣይ መስተካከል አለባቸው" ብለዋል።
በተለይም ከማዘጋጃ ቤት፣ ከመታወቂያ አሰጣጥ፣ ከንግድ ፣ ከግብር ስብሰባና ሌሎች ለሙስና ተጋላጭ የሆኑ አገልግሎቶችን ከእጅ መንሻ ነፃ የማድረግ ስራ በትኩረት ሊሰራ እንደሚገባ አሳስበዋል።
"ፐብሊክ ሰርቫንቱ ለህሊናው ተገዝቶ ቀልጣፋ፣ ግልፅና ከአድሎ የፀዳ አገልግሎት መስጠት ይገባዋል" ያሉት ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ፣ "በዚህም በጋራ በመረባረብ ክልላችንና ሀገራችንን ወደ ተሻለ ደረጃ ማሻገር ይጠበቅብናል" ብለዋል።
የክልሉ ፐብሊክ ሰርቪስ ቢሮ ሀላፊ አቶ አስረስ አዳሮ በበኩላቸው "የአገልጋይነት ቀንን ስናከብር ህዝብና ሀገርን በተሻለ መልኩ ለማሻሻል ራስን በማዘጋጀትና ለራስ ቃል በመግባት ሊሆን ይገባል" ብለዋል።
ለክልሉ መመስረት ዋነኛ ምክንያት የመንግስት አገልግሎት አሰጣጥ ተደራሽነት፣ መልካም አስተዳደርና የመልማት ጥያቄ መሆኑን አንስተው ተቋሙን ይህን ችግር መፍታት በሚያስችል መልኩ ሪፎም የማድረግ ስራ እየተሰራ መሆኑን አንስተዋል።
በዚህም የተገኙ ለዉጦች በየተቋማቱ የተለያየ ቢሆንም ተስፋ ሰጪ መሆኑን የጠቆሙት አቶ አስረስ፣ ተገልጋዩ በአቅራቢያዉ አገልግሎት እንዲያገኝ በሚያስችል መልኩ ከተሞችን በማደራጀት እየተሰራ መሆኑን አመልክተዋል።
የተሰጣቸውን ሀላፊነት በአገልጋይነት መርህ በመወጣት ቀልጣፋና ፈጣን አገልግሎት የሚሰጡ ሰራተኞችን የማበረታታ እንዲሁም አሰራርን ተከትለው የማይሰሩትን በተገቢዉ ለይቶ ከማረም አንፃር ክፍተቶች እንዳሉ ጠቁመው በተያዘው በጀት ዓመት ማስተካከያ እንደሚደረግ አመላክተዋል።
"በተያዘው በጀት አመት በሁሉም ተቋማት ጠንካራና ታታሪ ሰራተኞችን ከመለየትና ከማበረታታት እንዲሁም ወደኋላ የቀሩትን ደግፎ ከማብቃት አንፃር ትኩረት ተደርጎ ይሰራል" ብለዋል ።
በተቋማት በአገልግት አሰጣጥ ችግር መንስኤዎች አንዱ የሀሰት ማስረጃ ቅጥር መሆኑን ጠቁመው በተጠናቀቀው በጀት አመት በየደረጃው የተጀመረ የማጣራት ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል ።
ጳጉሜ አንድን ምክንያት በማድረግ ሁሉም ተቋማት እስከ ምሽቱ 1 ሰዓት ድረስ አገልግሎት እንደሚሰጥ አስታውቀዋል ።
የአገልጋይነት ትርጉምን በተገቢዉ ተረድቶ ህዝብና ሀገርን ማገልገል ክብር መሆኑን አንስተዉ፣ ጶጎሜ አንድን እስከ ምሽቱ አንድ ሰዓት ለማገልገል ዝግጁ መሆናቸዉን ተሳታፊዎቹ አንስተዋል።
በመድረኩ የመወያያ ሰነድ ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል ።
በመድረኩ ላይ ምክትል ርዕሰ መስተዳደር ዶክተር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾን ጨምሮ የክልል ቢሮ ሀላፊዎችና የሴክተር መስሪያ ቤቶች ስራተኞች ተገኝተዋል።