ቀጥታ፡

የኢትዮጵያውያን እሴት የሆነውን በትህትና ማገልገል እና መልካምነት በተቋሞቻችን ገቢራዊ በማድረግ ለሀገራችን ያለንን ፍቅር ማሳየት ይኖርብናል - ሚኒስትሮች

አዲስ አበባ ፤ ጳጉሜን 1/2015 (ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያውያን እሴት የሆነውን በትህትና ማገልገል እና መልካምነት በተቋሞቻችን ገቢራዊ በማድረግ ለሀገራችን ያለንን ፍቅር ማሳየት ይኖርብናል ሲሉ ሚኒስትሮች ገለጹ፡፡

ጳጉሜን 1 ቀን የአገልጋይነት ቀን ሆኖ እንዲከበር በተወሰነው መሰረት የተለያዩ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች ከ30 ዓመት እና ከዚያ በላይ ያገለገሉና በማገልገል ላይ ያሉ የመንግስት ሰራተኞች በተገኙበት የፓናል ውይይት ተደርጓል፡፡

የቱሪዝም ሚኒስትር አምባሳደር ናሲሴ ጫሊ እንደገለጹት፤ ኢትዮጵያውያን ከአያት ቅድመ አያቶቻችን የወረስነው በትህትና የማገልገል እሴት አለን፡፡

ኢትዮጵያውያን እንግዳ ተቀባይ ናቸው ሲባልም ተነሳሽነትን፣ ትህትናን፣ በእኩልነት ዝቅ ብሎ ማገለግልን፣ ጨዋነትና ፍትሐዊነትን የተላበሱ መሆናቸውን ማሳያ ነው ብለዋል፡፡
 

የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ዶክተር ዓለሙ ስሜ በበኩላቸው በርካቶች ለትምህርት ከሀገር ከወጡ በኋላ የተሻለ ኑሮ የሚመሩበትን ሥራ ጥለው በመመለስ ሀገራቸውን እንደሚያገለግሉ ገልጸዋል፡፡

ይህም አገርንና ህዝብን ማገልገል ሀብትና ንብረት ከማካበት በላይ የህሊና እርካታ የሚሰጥ መሆኑን ማሳያ ነው ብለዋል፡፡

ቀጣዩ አዲስ ዓመትም የኢትዮጵያ የሰላምና የብልጽግና ዘመን ይሆን ዘንድ ሁሉም አካላት በተሰማሩበት መስክ ባለጉዳዮችን በቅንነት ማገልገል ይገባቸዋል ብለዋል።
 

የጤና ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሰ የተገልጋዮችን ፍላጎት ለማርካት አገልጋዮች ፍጹም ጨዋ እና ርህራሔን የተላበሱ ሊሆኑ እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡

በተለይም በጤና ዘርፍ ህሙማን አገልጋዩ የማያውቃቸው ሌሎች ስሜትን የሚረብሹ ችግሮች ሊኖርባቸው ስለሚችል በህሙማን ቦታ ላይ ሆነው ማሰብ ይኖርባቸዋል ብለዋል፡፡

ከዚህም በተጨማሪ መሪዎችም ሆነ ባለሙያዎች አገልጋዮች በመሆናቸው በተሰማሩበት መስክ ስራውን ጠንቅቀው የሚያውቁ ብቃት ያላቸው መሆን ይኖርባቸዋል ብለዋል፡፡
 

የሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ዶክተር መኩሪያ ኃይሌ በበኩላቸው፤ ተቋማት መልካም የሰሩት የሚበረታቱበት ተገልጋይ የበደሉት የሚጠየቁበት አሰራርና የህግ ማዕቀፍ ማዘጋጀት አለባቸው ብለዋል፡፡

በተጨማሪም ውጤታማ አገልግሎት ለመስጠት የአቅም ግንባታ እንዲሁም የድጋፍና ክትትል ስራዎችን ማጠናከር እንደሚገባም ተናግረዋል።

እየተገባደደ ያለውን 2015 ዓ.ም በመሸኘት አዲሱን ዓመት ለመቀበል የጳጉሜን ቀናት በተለያዩ ስያሜዎች መሰየማቸው ይታወቃል።

በዚሁ መሰረት ጳጉሜን 1 የአገልጋይነት ቀን፣ ጳጉሜን 2 የመስዋዕትነት ቀን፣ ጳጉሜን 3 የበጎነት ቀን፣  ጳጉሜን 4 የአምራችነት ቀን፣ ጳጉሜን 5 የትውልድ ቀን እና ጳጉሜን 6 የአብሮነት ቀን ሲሆኑ የአገልጋይነት ቀን "ኢትዮጵያን እናገልግል" በሚል መሪ ሀሳብ በተለያዩ ዝግጅቶች እየተከበረ ይገኛል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም