ስለ አገልግሎታችሁ ኢትዮጵያ ታመሰግናችኋለች፣እኛም እናመሰግናችኋለን-ከንቲባ አዳነች አቤቤ

አዲስ አበባ፤ ጳጉሜን 1/2015 (ኢዜአ)፡-ስለ አገልግሎታችሁ ኢትዮጵያ ታመሰግናችኋለች፣እኛም እናመሰግናችኋለን ሲሉ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ።

ከንቲባ  አዳነች አቤቤ የ"አገልግሎት ቀን"ን አውቶቢስ ተራ መናሀሪያ በመገኘት አስጀምረዋል።

በመርሃ ግብሩ ላይ ከንቲባዋ ባስተላለፉት መልዕክት "በዚህ ሰዓት ተገኝቶ ማገልገል የእናንተ የዘውትር ስራችሁ ነው ፤ ሁሌም ደከመን ሰለቸን ሳትሉ ህዝባችሁን ስለምታገለግሉ ኢትዮጵያም እኛም እናመሰግናችኋለን" ብለዋል።

"ሌሎች ስራዎቻችን ውጤታማ እንዲሆኑ የእናንተ አገልግሎት ትልቅ ድርሻ አለው" ያሉት ከንቲባዋ "በ2016 ዓ.ም የበለጠ አገልግሎታችንን አልቀን በተሰማራንበት የስራ ዘርፍ በተገቢው ሁኔታ መከወን እንድንችል ኢትዮጵያን ከፍ ልናደርጋት ተገኝተናል" ሲሉ ተናግረዋል።

ከምንም በላይ ውድ የሆነውን የሰው ህይወት ለአደጋ እንዳይጋለጥ በመታደግ በኩል የእናንተ ስራ ትልቅ ሚና አለውም ብለዋል ከንቲባዋ።

በቀጣዩ ዓመት በዘርፉ ያሉ ክፍተቶች እንዳይቀጥሉና በአገልግሎት የላቀ ውጤት ለማስመዝገብ ሁሉም እንዲረባረብ ጥሪ አቅርበዋል።

ከንቲባዋ በዘርፉ ዋነኛ ችግር የሆነውን የትራፊክ አደጋ ለመቀነስ እና በ2016 በዜጎች ላይ የሚደርሰውን የህይወት፣ የአካል እና የንብረት ውድመት በመሰረታዊነት ለመቅረፍ ባለድርሻ አካላት ቃል እንዲገቡም ጠይቀዋል።

በዚህም የትራንስፖርት ዘርፍ ባለድርሻ አካላት ቃል የገቡበት መርሃ ግብር መካሄዱን የኤ ኤም ኤን ዘግቧል። 

 

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም