የተሽከርካሪ መለዋወጫዎችን ጨምሮ የተለያዩ ቁሳቁሶችን በሕገ-ወጥ መንገድ ሲያዘዋውሩ የነበሩ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር ዋሉ - የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ - ኢዜአ አማርኛ
የተሽከርካሪ መለዋወጫዎችን ጨምሮ የተለያዩ ቁሳቁሶችን በሕገ-ወጥ መንገድ ሲያዘዋውሩ የነበሩ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር ዋሉ - የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ
አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 30 /2015 (ኢዜአ)፡-በርካታ ሞባይሎችን፣ የተሽከርካሪ መለዋወጫዎችንና ሌሎች ቁሳቁሶችን በመኪና ሻግ በሕገ-ወጥ መንገድ ጭነው ሲያዘዋውሩ የነበሩ ሁለት ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ገለፀ፡፡
ሁለቱ ተጠርጣሪዎች ነሐሴ 26 ቀን 2015 ዓ.ም ለጊዜው ባለቤቱ ባልታወቀ ተሽከርካሪ 202 ፍየሎችን ከላይ፣ ከሥር ደግሞ በርካታ ሞባይሎችን፣ የተሽከርካሪ መለዋወጫዎችን፣ መድሃኒቶችን እና የብር ጌጣጌጦችን በሻግ ጭነው ከያቤሎ ወደ አዲስ አበባ ከተማ ሲያጓጉዙ በቁጥጥር ስር ውለዋል።
በአዲስ አበባ ጉላሌ ክፍለ ከተማ ልዩ ቦታው ብርጭቆ ፋብርካ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ እንደደረሱ የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ከብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ጋር በመተባበር ባደረገው ክትትል ከነ-ኤግዚቢቱ በቁጥጥር ሥር ውለው ምርመራ እየተጣራባቸው እንደሚገኙ ተገልጿል።
የወንጀል አፈፃፀም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየረቀቀ ቢመጣም የፀጥታ ተቋማት ከዘመኑ ጋር አብሮ እየዘመኑ ወንጀል ፈፃሚዎችን በቁጥጥር ሥር እያዋሉ መሆኑን ጠቅሶ ኅብረተሰቡ ከተቋማቱ ጎን በመቆም የተለመደ ትብብሩን አጠናክሮ እንዲቀጥልም መልዕክት አቅርቧል።