ቀጥታ፡

በሰመራ ሎጊያ ከተማ በ28 ሚሊዮን ብር ወጪ የተገነባ የጌጠኛ ድንጋይ ንጣፍ መንገድ አገልግሎት መስጠት ጀመረ

ሰመራ ፤ ነሐሴ 30/2015 (ኢዜአ) ፦በአፋር ክልል ሰመራ ሎጊያ ከተማ በ28 ሚሊዮን ብር ወጪ የተገነባ የጌጠኛ ድንጋይ ንጣፍ መንገድ ተመርቆ አገልግሎት መስጠት ጀመረ። 

ዛሬ መንገዱን መርቀው ለአገልግሎት ክፍት ያደረጉት በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የአፋር ክልል ማህበራዊ ጉዳዮች ክላስተር አስተባባሪ ወይዘሮ አሚና ሴኮ እና ሌሎች የክልሉ አመራሮች ናቸው።
የከተማ አስተዳደሩ ከንቲባ አቶ አብዱ ሙሣ በምረቃው ሥነ ሥርዓት ላይ ለመንገዱ ግንባታ የዋለው ወጪ ከከተሞች የተቀናጀ ልማት ፕሮጀክት (ዩ.አይ.ዲ.ፒ)፣ ከአስተዳደሩ ገቢ እና ከሌሎች ምንጮች መሸፈኑን አስታውቀዋል። 

በከተማዋ የተለያዩ አቅጣጫዎች ላይ የሚገኙ መንደሮችን በቅርበት የሚያገናኘው መንገድ ተሽከርካሪዎችን በሁለት አቅጣጫዎች ለመጓጓዝ እንደሚያስችልም ገልጸዋል።

ዛሬ ለአገልግሎት የበቃው መንገድ 1 ነጥብ 7 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው ሲሆን ከተማዋን ጽዱና ሳቢ ለማድረግ የራሱ አስተዋጽኦ እንዳለውም አቶ አብዱ ተናግረዋል።

የከተማው ነዋሪዎች ለመንገዱ ግንባታ የጉልበት አስተዋጽኦ በማድረግ መሳተፋቸውን ገልጸዋል።


 

በከተማዋ ተመሳሳይ የጌጠኛ ድንጋይ ንጣፍ መንገዶች ግንባታ በቀጣይነት በስፋት እንደሚካሄድም ከንቲባው አስታውቀዋል።

የመንገዱ ግንባታ በሦስት ወራት ጊዜ ውስጥ እንደተከናወነና በሥራውም በርካታ ሰዎች መሳተፋቸውን አቶ አብዱ ተናግረዋል። 

በከተማው በንግድ ሥራ የተሰማሩት አቶ መሐመድ አመሊ በበኩላቸው መንገዱ ሥራቸውን ለማከናወን ምቹ ሁኔታ እንደፈጠረላቸው ገልጸዋል።

ወጣት ኩልሰማ ዓሊ የተባለች ነዋሪ በበኩሏ በመንገድ ሥራው በሥራ ዕድል ተሳታፊ እንደነበረች ጠቅሳ፣ ግንባታው ተጠናቅቆ ለአገልግሎት በመብቃቱ መደሰቷን ተናግራለች። 

መንገዱ መሰራቱ በተለይ ሕሙማንን ወደጤና ተቋማት ፈጥኖ ለማድረስ እንደሚያስችል የገለጸው ደግሞ በከተማዋ በባጃጅ አሽከርካሪነት የተሰማራው ወጣት ታምራት ይመር ነው፡፡

ሌላው የከተማው ነዋሪ አቶ ሄለም መሐመድ መንገዱ በከተማው መሃል መገንባቱ ለከተማዋ ገጽታ ካለው ጠቀሜታ ባለፈ በምቹ መንገድ ለመጓዝ ያስችለናል ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል። 
 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም