ቀጥታ፡

በአገር አቀፍ ደረጃ ከስድስት ሚሊዮን በላይ አርሶና አርብቶ አደሮች የዲጂታል ግብርና አገልግሎት ተጠቃሚ ሆነዋል - የኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት

አዲስ አበባ ፤ ነሐሴ 30/2015 (ኢዜአ) ፦በአገር አቀፍ ደረጃ  ከስድስት ሚሊዮን በላይ አርሶና አርብቶ አደሮች የዲጂታል ግብርና አገልግሎት ተጠቃሚ መሆናቸውን የኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት አስታወቀ።

ዓለም በዲጂታል ቴክኖሎጂው ይበልጥ አንድ እየሆነች በመጣችበት በዚህ ወቅት አገራት ቴክኖሎጂዎችን ከግብርና ባህሪይ ጋራ በማጣጣም ጥቅም ላይ እያዋሉ ይገኛሉ፡፡

በዚህም ሰው ሰራሽ አስተውሎት፣ሮቦቶች፣ ሰው አልባ አውሮፕላኖች፣ መረጃን የሚተነትኑ ቴክኖሎጂዎችና ሌሎች የዲጂታል አማራጮች የግብርናው ዘርፍ አሰራር የማቀላጠፍ ሚና እየተወጡ ይገኛሉ፡፡

በኢትዮጵያም የግብርናውን ዘርፍ በዲጂታል አሰራር ለማዘመን የተለያዩ ጥረቶች እየተደረጉ ሲሆን በሚያዚያ ወር 2015 ወደ ስራ የገባው የኢትዮጵያ የዲጂታል ግብርና ፍኖተ ካርታ በማሳያነት ይጠቀሳል።

ፍኖተ ካርታው አርሶ አደሮችና አርብቶ አደሮች የዲጂታል አገልግሎቶችን በመጠቀም ምርታማነታቸውን እንዲጨምሩ የሚያግዝ ነው፡፡

የኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት የኮሜርሻይላዜሽን ፕሮግራም ሲኒየር ዳይሬክተር ዶክተር ዳኛቸው ሉሌ፤ በ8028 ነጻ የስልክ መስመር ከ6 ነጥብ 3 ሚሊዮን በላይ አርሶና አርብቶ አደሮች የተለያዩ የግብርና መረጃዎች በተለያዩ ቋንቋ አማራጮች የ24 ሰዓት አገልግሎት እየተሰጣቸው መሆኑን ለኢዜአ ገልጸዋል።

በዚህም የየአካባቢውን ስነ ምህዳር መሰረት በማድረግ የግብዓት አጠቃቀም፣የአዘራር ዘዴ፣ የበሽታዎችና የተባዮዎች መከላከል፣የምርት አሰባሰብና አያያዝና የአየር ጠባይ ሁኔታ የመሳሰሉ መረጃዎች ተደራሽ እየሆኑ እንደሚገኝ አመልክተዋል።

በተጨማሪም በ6077 ''አገር አቀፍ የገበያ መረጃ ማዕከል'' አማካኝነት አርሶ አደሮች የግብርና ምርት መረጃ እያገኙ ነው ብለዋል።

በተያዘው በጀት ዓመት ደግሞ የነጻ የስልክ መስመሮችን ከኢንተርኔት ጋር በማገናኘት ዲጂታላይዝ መደረጋቸውን ተናግረዋል።

በዚህም አርሶ አደሮች በእጅ ስልካቸው የተሟላ መረጃ እንዲደረሳቸው ብሔራዊ የገበያ መረጃ ስርዓት(NMIS) ተግባራዊ መሆኑንም ነው ዶክተር ዳኛቸው ያስረዱት።

አርሶ አደሮች በስርዓቱ አማካኝነት ከምርት ሂደት እስከ ገበያ ድረስ የተሟላ መረጃ ከመስጠቱ በላይ በአየር ንብረት ለውጥ ሆነ በተለያዩ ምክንያት በምርታማነት ላይ ጉዳት የሚያደርስ ክስተቶች ላይ የቅድመ ማስጠንቀቂያ መረጃ እያገኙ ነው ብለዋል።

ኢንስቲትዩቱ ባለሙያዎቹን በተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች በማሰማራት በዓለም አቀፍ የቦታ አቀማመጥ ስርዓት(ጂፒኤስ) እና በመልክዓ ምድራዊ የመረጃ ስርዓት(ጂአይኤስ) ለአርሶ አደሩ የሚያስፈልጉ መረጃዎችን እየሰበሰበ እንደሚገኝም አመልክተዋል።

የመረጃ ስርዓቶቹ መረጃን ከመሰብሰብ ባለፈ ባለሙያዎች የሚልኳቸው መረጃዎች መሬት ካለው ነባራዊ እውነታ ጋር የሚዛመዱ መሆናቸውን እንደሚያረጋግጡም ነው ያብራሩት።

ዲጂታል ግብርና ትክክለኛና ዘላቂ የመረጃ ትንተና ላይ የተመሰረቱ ፈጣን ውሳኔዎችን በመስጠት ምርትና ምርታማነት እንዲጨምር እንደሚያደርግ የዘርፉ ባለሙያዎች ይገልጻሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም