ቀጥታ፡

የኃይማኖት ተቋማት ባላቸው አስተምህሮ መሰረት በጳጉሜን ወር ለሶስት ቀናት የጸሎትና የንሰሀ መርሃ ግብር  ሊያካሄዱ ነው

አዲስ አበባ ፤ ነሐሴ 30/2015 (ኢዜአ) ፦ የኃይማኖት ተቋማት ባላቸው አስተምህሮ መሰረት በጳጉሜን ወር ለሶስት ቀናት የጸሎትና የንሰሀ መርሃ ግብር የሚያካሄዱ መሆኑን የኢትዮጵያ ኃይማኖት ተቋማት ጉባኤ አስታወቀ።  

የኢትዮጵያ  ኃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ጠቅላይ ፀሀፊ ሊቀ ትጉሃን ቀሲስ ታጋይ ታደለ፤ የጸሎትና የንሰሀ መርሀ ግብሩን በማስመልከት መግለጫ ሰጥተዋል።

በመግለጫቸውም መርሃ ግብር "ጥላቻ የራቀበት፣ የፍቅር ብሩህ ተስፋ የሚታይበት አዲስ ዓመት በንሰሃና እና በይቅርታ እንቀበል" በሚል መሪ ሃሳብ የሚካሄድ መሆኑን ገልጸዋል።     

በመሆኑም ከጳጉሜን 3 እስከ 5 ቀን 2015 ዓ.ም የሃይማኖት ተቋማት በየእምነቶቻቸው አስተምህሮ መሰረት ብሄራዊ የጸሎትና የንሰሀ መርሀ ግብር ያካሂዳሉ ብለዋል።  

የጸሎትና የንሰሀ ፕሮግራሙ ዓላማም በሰዎች ዘንድ አብሮነትን፣ መተሳሰብና መተጋገዝን በማጽናት  የሚገጥሙ ፈተናዎቸን በይቅርታ እና በእርቅ መፍታትን ያለመ መሆኑን አብራርተዋል። 

ለዚህም የሀይማኖት ተቋማት ለተከታዮቻቸው ስለ ይቅርታ፣ ንሰሀና እርቅ አባቶች በሰፊው ትምህርት ይሰጣሉ ብለዋል።

በመጨረሻው መርሃ ግብር  ጳጉሜን 5 ከቀኑ 7 ሰዓት ጀምሮ በወዳጅነት አደባባይ የሀይማኖት አባቶች፣ ከፍተኛ የመንግሥት የስራ ሃላፊዎች እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በተገኙበት ተመሳሳይ ተግባራት ይከናወናሉ ሲሉ ተናግረዋል።  

የኢትዮጵያን ዘላቂ ሰላም ለማረጋገጥ ሁላችንም በአብሮነት፣ በመተባበርና በመተጋገዝ በጋራ እንቁም በማለት መልእክታቸውን አስተላልፈዋል።  


 

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሀፊ እና የኒዎርክ እና አካበቢው  ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ዶክተር አቡነ ጴጥሮስ፣ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ሼኸ ሀጂ ኢብራሂም ቱፋ እና የኢትዮጵያ ካቶሎካዊት ቤተ ክርስቲያን የትምህርት ክፍል ሀላፊ አባ ዳንኤል ሀሶ፤ ምእመናን በየሃይማኖታቸው የጸሎትና የንሰሀ መርሀ ግብር ላይ በመገኘት ለሀገራቸው ሁለንተናዊ ሰላም እና አንድነት የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።  


 

የኢትዮጵያ ወንጌላዊያን  አብያተ ክርስቲያናት ህብረት ምክትል ፕሬዝዳንት ፓስተር ሰንበቶ በሼ እና የኢትዮጵያ ወንጌላዊት ቤተክርስቲያን መካነ እየሱስ ፕሬዚዳንት ቄስ ዶክተር ዮናስ ይገዙ፤ ተመሳሳይ መልእክቶቻቸውን አስተላልፈዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም