ቀጥታ፡

በሐረሪ ክልል በ100 ሚሊዮን ብር ወጪ የተገነቡ የልማት ፕሮጀክቶች ተመርቀው ለአገልግሎት በቁ

ሐረር (ኢዜአ) ነሐሴ 30/2015 ፦በሐረሪ ክልል በ100 ሚሊዮን ብር ወጪ የተገነቡ የተለያዩ የልማት ፕሮጀክቶች ዛሬ ተመርቀው ለአገልግሎት በቁ። 

በክልሉ ገጠር ወረዳዎች የተገነቡትን ፕሮጀክቶች የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪ፣ በብልጽግና ፓርቲ የሐረሪ ክልል ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ አብዱልጀባር መሐመድ እና ሌሎች የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች መርቀዋቸዋል።

በክልሉ ኤረር እና በሶፊ ወረዳዎች ተገንብተው ዛሬ ለምረቃ የበቁት ድልድይ፣ የንፁህ መጠጥ ውሃና የኤሌክትሪክ መስመር ፕሮጀክቶች ናቸው።

የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክቶቹ የወረዳዎቹን ከ7ሺህ 400 በላይ የሚሆኑ አባወራዎች ተጠቃሚ እንደሚያደርጉ ተገልጿል። 

ሌላው በኤረር ወረዳ 18 መንደሮችን ተጠቃሚ የሚያደርገው የኤሌክትሪክ ኃይል መሥመር ዝርጋታ 55 ሚሊዮን ወጪ እንደተደረገበት ተመልክቷል።

በወረዳው ሳምቴ ወንዝ ላይ የተገነባው 20 ሜትር ርዝመት ያለው ድልድይም ተመርቋል።

አቶ ኦርዲን በዚህ ወቅት እንደተናገሩት የክልሉ መንግስት በክልሉ ፍትሃዊ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ በከተማና በገጠሩ ያለውን የልማት ፍላጎት ለማሟላት እየሰራ ነው።

በተለይ የአርሶ አደሩ ምርትና ምርታማነት እና የህዝቡን የልማት ተጠቃሚነት ለማሳደግ የሚካሄዱ የልማት ሥራዎች በቀጣይም ተጠናክረው ይቀጥላሉ ብለዋል።

በብልጽግና ፓርቲ የሐረሪ ክልል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ አብዱጀባር መሀመድ በበኩላቸው የክልሉ ሕዝብ ከመንግሥት ጎን ሆኖ እያደረገ ያለውን ድጋፍ አጠናክሮ እንዲቀጥል አሳስበዋል።

ፕሮጀክቶቹ ለረጅም ጊዜ አገልግሎት እንዲሰጡ ህብረተሰቡ ተገቢውን ጥበቃና እንክብካቤ እንዲያደርግም ጠይቀዋል።

ፕሮጀክቶቹ ለአገልግሎት በበቁባቸው አካባቢዎች ያሉ ነዋሪዎች በበኩላቸው መሰረተልማቶቹ ከዚህ በፊት ይገጥሟቸው የነበሩትን ችግሮች እንዳቃለሉላቸው ተናግረዋል።

በምረቃ መርሃ ግብሩ ላይ የክልሉ መንግሥት ከፍተኛ አመራሮችና የአካባቢው ነዋሪዎች ተገኝተዋል።

 

 
 
 
  

 

 

 

   

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም