በአስተዳደሩ ለዘመን መለወጫ በዓል የሚውሉ ምርቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ ለማቅረብ ዝግጅት ተደርጓል---ቢሮው - ኢዜአ አማርኛ
በአስተዳደሩ ለዘመን መለወጫ በዓል የሚውሉ ምርቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ ለማቅረብ ዝግጅት ተደርጓል---ቢሮው
ድሬዳዋ (ኢዜአ) ነሐሴ 30/2015--በድሬዳዋ አስተዳደር ለመጪው የዘመን መለወጫ በዓል ምርቶች በተመጣጣኝ ዋጋ ለማቅረብ ዝግጅት መደረጉን የአስተዳደሩ ንግድ፣ ኢንዱስትሪ እና ኢንቨስትመንት ቢሮ ገለጸ።
በዓሉን ምክንያት በማድረግ የዋጋ ጭማሪ በሚያደርጉ ነጋዴዎች ላይ ሕጋዊ እርምጃ ለመውሰድ ግብረሀይል ተቋቁሞ ወደ ሥራ መግባቱም ተመላክቷል።
በቢሮው የንግድ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አሚኖ ጣሃ በሰጡት መግለጫ እንዳሉት፣ አስተዳደሩ ምርቶችን በበቂ ሁኔታ ለህብረተሰቡ ለማቅረብ እየሰራ ነው።
ለእዚህም ቦሮው ከፌዴራል ተቋማትና በአስተዳደሩ ከሚገኙ የሸማቾች ኅብረት ሥራ ማህበራት ጋር ተቀናጅቶ እየሰራ ይገኛል ብለዋል።
በአስተዳደሩ በከተማና በገጠር 13 ወረዳዎች የሚገኙ መሠረታዊ የሸማቾች ኅብረት ሥራ ማህበራት ምርቶችን ለማቅረብ ዝግጅት ማድረጋቸውን ገልጸዋል።
ማህበራቱ ለበዓሉ የተዘጋጁትን 455 ሺህ ሊትር የምግብ ዘይት እና 933 ኩንታል ስኳር በተመጣጣኝ ዋጋ ለህብረተሰቡ እንደሚያከፋፍሉም አመልክተዋል።
"በተጨማሪ በዓሉን ምክንያት በማድረግ ሳምንቱን በሙሉ የግብርናና የኢንዱስትሪ ምርቶች በቅዳሜና እሁድ ገበያ በበቂ መጠን ለሸማቹ እንዲቀርቡ ይደረጋል" ያሉት አቶ አሚኖ፣ የንግድና ባዛር ኤግዚቢሽን መዘጋጀቱንም ጠቁመዋል።
ከተጎራባች ክልል የቁም እንስሳትን ለማስመጣት እየተሰራ መሆኑን የገለጹት ኃላፊው፣ በዓልን ምክንያት በማድረግ ተጋነነ የዋጋ ጭማሪ እንዳይከሰት ቀድሞ የመከላከል ሥራ እንደሚሰራ አስታውቀዋል።
በፍራንኮ ቫሉታ የሚገቡ መሠረታዊ የፍጆታ ምርቶችን የሚያቀርቡ አካላትም ከተፈቀደው ትርፍ በላይ የዋጋ ጭማሪ ማድረግ እንደማይችሉ አስገንዝበዋል።
"ምርቶችን በመጋዘን አከማችተው እጥረት እንዲፈጠር በሚያደርጉ እና የተጋነነ የዋጋ ጭማሪ በሚያደርጉ አካላት ላይ ህጋዊ እርምጃ ይወሰዳል" ብለዋል።
በመሆኑም ግብረ ኃይል ተቋቁሞ ወደ ሥራ መግባቱን ነው አቶ አሚኖ ያስታወቁት።
ህብረተሰቡ ሰው ሰራሽ የምርት እጥረት በሚፈጥሩና የተጋነነ የዋጋ ጭማሪ የሚያደርጉ ሲገጥሙት ለፖሊስ በመጠቆም የበኩሉን እንዲወጣም አሳስበዋል።
ከፍጆታ ምርቶች ጋር ባዕድ ነገር ቀላቅለው የህዝብን ጤና የሚጎዱ ስግብግብ ነጋዴዎችን በማጋለጥ ትብብሩን እንዲያሳይም ኃላፊው አስገንዝበዋል።