ቀጥታ፡

ኮርፖሬሽኑ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ከ7 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ ማግኘቱን ገለጸ

አዲስ አበባ ፤ ነሐሴ 30/2015 (ኢዜአ) ፦ የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ስራዎች ኮርፖሬሽን በ2015 በጀት ዓመት ከ7 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ ማግኘቱን አስታወቀ።    

ኮርፖሬሽኑ የ2015 በጀት ዓመት የእቅድ አፈጻጸም የውይይት መድረክ አካሂዷል።

የኮርፖሬሽኑ ዋና ስራ አስፈጻሚ ኢንጂነር ዮናስ አያሌው በዚሁ ጊዜ፤ ተቋሙ የአቅም ግንባታ፣የፕሮጀክት አስተዳደር፣ዲጂታላይዜሽንና ኢንዱስትሪ ተኮር ማሻሻያዎችን በማድረግ የተሻለ ለውጥ ማምጣት መቻሉን አመልክተዋል።

በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ተቋሙ 8 ነጥብ  49 ቢሊዮን ብር ገቢ ለማግኘት አቅዶ 7 ነጥብ 12 ቢሊዮን ብር ማግኘቱን ጠቁመዋል።

በበጀት ዓመቱ ኮርፖሬሽኑ ከታክስ በፊት የ669 ነጥብ 8 ሚሊዮን አጠቃላይ ትርፍ ማግኘቱንም ጠቅሰው በዚህም የእቅዱን 83 ነጥብ 8 በመቶ ማሳካት መቻሉን ነው የተናገሩት።


 

ኮርፖሬሽኑ ከ56 ቢሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ እየገነባቸው ካሉ 80 ፕሮጀክቶች መካከል 24ቱን  በተጠናቀቀው በጀት ዓመት በማጠናቀቅ ማስረከቡን አመልክተዋል። 

በግንባታ ላይ ካሉት ቀሪ 56 ፕሮጀክቶች መካከል 22ቱ  በተጠቀሰው በጀት ዓመቱ ውል ተፈርሞባቸው ወደ ስራ የገቡ መሆናቸውንም ጠቁመዋል።

የውጪ ምንዛሬ እጥረት፣የወሰን ማስከበር ችግሮች፣ሲሚንቶን ጨምሮ ሌሎች ግብዓቶች በሚፈለገው መጠን አለመሟላትና የስራ ክፍያዎች መዘግየት በበጀት ዓመቱ ካጋጠሙ ችግሮች መካከል እንደሚጠቀሱም ነው ዋና ስራ አስፈጻሚው ያነሱት።
 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም