የጳግሜን ቀናት ስያሜዎች ለአገር ግንባታና አንድነት መጠናከር አዎንታዊ ሚና አላቸው - ዶክተር መብራቱ ዓለሙ - ኢዜአ አማርኛ
የጳግሜን ቀናት ስያሜዎች ለአገር ግንባታና አንድነት መጠናከር አዎንታዊ ሚና አላቸው - ዶክተር መብራቱ ዓለሙ
አዲስ አበባ ፤ ነሐሴ 30/2015 (ኢዜአ) ፦ የጳግሜን ቀናት ስያሜዎች ለአገር ግንባታና አንድነት መጠናከር አዎንታዊ ሚና እንዳላቸው የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሥራ አስፈጻሚ አባል ዶክተር መብራቱ ዓለሙ ተናገሩ።
የጳጉሜን ወር ቀናት የዜጎችን የአብሮነት እሴት፣ የአገልጋይነት ባህልና ስሜትን እንዲሁም ሕብረ ብሔራዊ አንድነትን በሚያጸና መልኩ እንደሚከበሩ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት መግለጹ ይታወሳል።
ይህንንም ተከትሎ፤ ጳግሜን 1- የአገልግሎት ቀን፣ ጳግሜን 2- የመስዋእትነት ቀን፣ ጳግሜን 3- የበጎነት ቀን፣ ጳግሜን 4- የአምራችነት ቀን፣ ጳግሜን 5- የትውልድ ቀንና ጳግሜን 6- የአብሮነት ቀን በሚል ተሰይመው የሚታሰቡ ይሆናል።
በስያሜዎቹ አንድምታና ፋይዳዎች ዙሪያ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሥራ አስፈጻሚ አባል ዶክተር መብራቱ ዓለሙን አናግሯል።
ዶክተር መብራቱ እንደገለጹት፤ የጳግሜን ቀናት ሥያሜዎች ሁሉም የአገሪቱ ዜጋ ለአገር ግንባታና አንድነት መጠናከር አዎንታዊ ሚናውን እንዲጫወት ያስችላሉ።
በአዲሱ ዓመት በማኅበራዊና ፖለቲካዊ መስኮች የሚጠበቀው ለውጥ እንዲመጣ የእነዚህን ቀናት ሥያሜዎች ወደ መሬት በማውረድ መሥራት ይገባልም ብለዋል።
ለአብነትም የአገልግሎት ቀን በመሆኑ በቅንነት ያገለገሉ አገር ወዳዶችን ማመስገን፣ ማስታወስና እውቅና መስጠት ለቀጣይ ሥራዎች መሰረት የሚጥሉ ናቸው ብለዋል።
ከዚህ ባሻገርም አገልግሎት አሰጣጥ ጋር የተያያዙ ችግሮችን ፈትሾ መፍትሄ ማበጀት ለቀጣይ የአገር ዕድገት መሳለጥ ፋይዳው የላቀ መሆኑንም አስገንዝበዋል።
"የህዳሴ ግድብን ጨምሮ ትልልቅ የመንግሥት ፕሮጀክቶች ከዳር እንዲደርሱ ሁሉም መስዋዕትነት መክፈል ይጠበቅበታል" ያሉት ዶክተር መብራቱ የአገር ዕድገት እንዲቀጥል ጊዜንና ጉልበትን መስዋዕት አድርጎ መሥራት እንደሚጠይቅም አብራርተዋል።
ከበጎነት ቀን ጋር በተያያዘ የተቸገሩትን ከመጎብኘት፣ አቅመ ደካሞችን ከማገዝ ባለፈ በጎነትን ባሕል ማድረግ እንደሚገባም አጽንኦት ሰጥተዋል።
በአምራችነት ቀን፤ ኢትዮጵያ የበርካታ የተፈጥሮ ኃብት ባለቤት መሆኗ ይታወስባታል ብለዋል።
በዚህም የሥራ ባህልን በማሳደግና የግብዓት አቅርቦት ችግሮች በመፍታት ምርታማነት ለማሳደግ መሥራት እንደሚገባ አጽንዖት መስጠት እንደሚገባ ተናግረዋል።
በአብሮነት ቀን በአገሪቷ የሚስተዋለውን የፖለቲካ መገፋፋትና ቁርሾ ወደ ጎን በመተው የሰለጠነ የፖለቲካ ባህል መገንባት እንደሚገባ አማላካች ነው ብለዋል።
በኢትዮጵያ የተረጋጋ ፖለቲካና ኢኮኖሚ መገንባት፤ አቃፊነትን ጨምሮ የመቻቻል ፖለቲካ ሥርዓት መገንባት ወሳኝ ሚና እንደሚኖረውም ነው የተናገሩት።
አዲስ ዓይነትና የተሻለ የፖለቲካ ባህል ለመዘርጋት ምሁራን፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች የአገር ሽማግሌዎች የበኩላቸውን ሚና ሊወጡ እንደሚገባም አመልክተዋል።
ለአብሮነት መጎልበት መተባበርና ባህላዊ እሴቶችን ማጠናከር ወሳኝ መሆኑንም አስምረውበታል።
በኢትዮጵያ የሚስተዋሉ ዘርፈ ብዙ ችግሮች ሁነኛ መፍትሄ ለመስጠት በጋራ መረባረብ ያስፈልጋል ብለዋል።