መንግስት የአየር ንብረት ለውጥ ችግርን ለመቅረፍ ስትራቴጂ ነድፎ እየሰራ ነው-ዶክተር ፍጹም አሰፋ - ኢዜአ አማርኛ
መንግስት የአየር ንብረት ለውጥ ችግርን ለመቅረፍ ስትራቴጂ ነድፎ እየሰራ ነው-ዶክተር ፍጹም አሰፋ
አዲስ አበባ ፤ ነሐሴ 30/2015 (ኢዜአ) ፦ የኢትዮጵያ መንግስት የአየር ንብረት ለውጥ ችግርን ለመቅረፍ ስትራቴጂ ነድፎ እየሰራ መሆኑን የፕላንና ልማት ሚኒስትር ዶክተር ፍጹም አሰፋ ገለጹ።
የአፍሪካ የአየር ንብረት ጉባኤ በኬንያ ናይሮቢ ከተማ እየተካሄደ ይገኛል።
የፕላንና ልማት ሚንስትር ዶክተር ፍጹም አሰፋ በዚሁ መድረክ ላይ ተገኝተው በጉዳዩ ዙሪያ ሀሳባቸውን ማካፈላቸውን የሚኒስቴሩ መረጃ ይጠቁማል።
በዚህም የአየር ንብረት ለውጥ ፋይናንስ ዙሪያ እና የጉባኤው ውጤት ሊሆኑ በሚገባቸው ጉዳዮች ላይ የኢትዮጵያን ጥረት እና በዓለም አቀፍ ደረጃ ያሉ ክፍተቶችን በማሳየት መደረግ በሚገባቸው ጉዳዮች ላይ ሀሳባቸውን አጋርተዋል፡፡
በናይሮቢ እየተካሄደ በሚገኘው የአፍሪካ የአየር ንብረት ጉባኤ ዶክተር ፍጹም አሰፋ በተባበሩት መንግስታት የአፍሪካ የኢኮኖሚ ኮሚሽን በተዘጋጀው በአየር ንብረት ፋይናንስ ላይ በተደረገው የውይይት መድረክ ሀሳባቸውን አቅርበዋል።
በዚህም በመንግስት በጀት ግምታቸው 82 ቢሊዮን ብር የሚሆኑ ፕሮጀክቶችና ፕሮግራሞች መተግበራቸውን መግለጻቸው በመረጃው ተመላክቷል።
እ.አ.አ. በ2019 በውጫዊ አጥኝ አካል ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር አረንጓዴ ኢኮኖሚ ስትራቴጂ የአፈጻጸም ግምገማ መከናወኑን በመጥቀስ አስረድተዋል፡፡
ጥናቱም ለአየር ንብረት ለውጥ ማጣጣሚያ ከዋለው በጀት አብዛኛው ከመንግስት ሲሆን ከዓለም ዓቀፍ ድጋፍ የተገኘው ቀጥሎ ያለውን ቦታ እንደሚያግዝ ገልጸዋል።
ከግል ተቋማት በአየር ንብረት ለውጥ ኢንቨስት የተደረገው እዚህ ግባ የሚባል እንዳልሆነ በማከል፡፡
በኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥ ዋነኛ የዕድገት ማነቆ ሆኖ ያለ ችግር መሆኑን መንግስት መረዳቱንና አስፈላጊውን ምላሽ ለመስጠት እየሰራ እንደሚገኝ ጠቅሰዋል።
ለዚህም ሀገራዊ የአየር ንብረት ለውጥ ማጣጣሚያ እቅድ እና እ.አ.አ እስከ 2050 የሚተገበር የረጅም ጊዜ የአነስተኛ ካርቦን ልቀት እና ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር የልማት ስትራቴጂ በመንደፍ ተግባር ላይ እያዋለ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በተጨባጭ በተግባር እየዋሉ ካሉ መርሃ ግብሮች ውስጥ የአረንጓዴ አሻራ አንዱ መሆኑን ገልጸው ኢትዮጵያ ባለፉት አራት ዓመታት ብቻ 25 ቢሊዮን የደን፣ የመኖና ለምግብነት የሚውሉ የፍራፍሬ ዝርያዎችን በመትከል የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል እየሰራች ለመሆኑ በማሳያነት አንስተዋል።
ከዚህ ጥረት ጎን ለጎን ኢትዮጵያ ራሷን በምግብ ለመቻል የምታደርገውን ጥረት እንዲደግፍ ታስቦ እየተሰራ መሆኑንም ዶክተር ፍጹም ጨምረው ገልጸዋል፡፡
የአረንጓዴ አሻራ፤ ውሃችን፣ የኃይል ምንጫችን፣ የኢኮኖሚ አውታራችን ሁሉ የተሳሰረበት መሆኑን የገለጹት ሚንስትሯ ተነሳሽነቱ ለጎረቤት ሀገራትም ትሩፋት ነው ብለዋል፡፡
በመሆኑም ሁሉም ድጋፍ ሊያደርግ ይገባልም ሲሉም አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡
ይሁንና በዓለም አቀፍ ደረጃ ያለው የገንዘብ ስሪት እና መዋቅር ሀገራት የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል የሚያደርጉትን ጥረት የሚያደናቅፍና በብድር አዙሪት ውስጥ እንዲቆዩ የሚያደርግ በመሆኑ ስር ነቀል የሆነ ማሻሻያ ሊደረግ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
ዶክተር ፍጹም አሰፋ የአፍሪካ የአካባቢ ሚንስትሮች ፕሬዝዳንት እንደመሆናቸው በቅርቡ ከነሐሴ 8 እስከ 12/2015 በአዲስ አበባ በተካሄደው የአፍሪካ የአካባቢ ሚንስትሮች ኮንፍረንስ የተወሰኑ ውሳኔዎች አሁን በረቀቀውና የአፍሪካ የአየር ንብት ጉባኤ ዋና ውጤት ይሆናል ተብሎ በሚጠበቀው የናይሮቢ ዲክላዴሽን ግምት ውስጥ እንዲገባ ጠይቀዋል።
በተጨማሪም የ28ኛው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ የአፍሪካ ሀገራት አቋም ዋነኛ መነሻ መሆን እንዳለበትም አስገንዝበዋል፡፡
የአፍሪካ የአየር ንብረት ጉባኤ በሀገራት መሪዎች ደረጃ በተለያዩ አጀንዳዎች እየመከረ የሚቀጥል ይሆናል፡፡