ቀጥታ፡

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የኢንቨስትመንት ዘርፉን ለእድገት ተገቢውን አስተዋጽኦ እንዲያበረክት ይደረጋል - ቢሮው

አሶሳ ፤ ነሐሴ 29/2015 (ኢዜአ)፡- በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ዘርፉን ለምጣኔ ሀብት አድገት ተገቢውን አስተዋጽኦ  እንዲያበረክት ልዩ ትኩረት እንደተሰጠው የክልሉ ኢንዱስትሪ እና ኢንቨስትመንት ቢሮ ገለጸ፡፡

የቢሮው  ሃላፊ አቶ ቃሲም ኢብራሂም ዛሬ በሰጡት መግለጫ እንዳመለከቱት ፤ የክልሉን እምቅ የተፈጥሮ ሃብት ለማልማት የተደረጉ ጥረቶች ቢኖሩም በሚፈለገው ልክ አይደለም፡፡

የኢንዱስትሪውንና ኢንቨስትመንት  ዘርፍ  ክልሉ ያለውን የተፈጥሮ ሀብት በመጠቀም ለምጣኔ ሀብት እድገት ተገቢው  አስተዋጽኦ እንዲያበረክት በተያዘው የበጀት ዓመት ልዩ ትኩረት እንደተሰጠው አስረድተዋል፡፡

በዚህም  በክልሉ አሶሳ ከተማ ለኢንዱስትሪ ፓርክ የሚውል 300 ሄክታር መሬት አስፈላጊው ጉዳይ ተሟልቶለት እየተዘጋጀ ሲሆን በዚህ ሳምንት ስራው ተጠናቆ ዝግጁ ይሆናል ብለዋል፡፡

በክልሉ የኢትዮጵያ ታምርት ፕሮግራም  ለመጀመሪያ ጊዜ እንደሚካሄድ የሚጠበቅ መሆኑን ጠቁመው፤  በተለያዩ ችግሮች የተዳከሙ ኢንዱስትሪዎችን ማጠናከርና ስራ ያቆሙትን ወደ ስራ የሚገቡበት ሁኔታ እንደሚመቻቸ ተናግረዋል፡፡

በዚህ ረገድ በክልሉ የዱቄት፣ የዘይት እንዲሁም በአነስተኛና ጥቃቅን ዘርፍ የሚካሄዱ አነስተኛ ኢንዱስትሪዎችን  ጠቅሰዋል፡፡

በክልሉ የሚገኙ የኢንዲስትሪ ዘርፍ ባለሙያዎችን አቅም በማጠናከር ለዘርፉ ተገቢውን ድጋፍ እንዲሰጡ እንደሚደረግ አቶ ቃሲም ገልጸዋል፡፡

እንዲሁም በክልሉ ለተለያዩ ኢንቨስትመንቶች የሚውል 79 ሺህ ሄክታር መሬት ተዘጋጅቶ ለአልሚ ባለሃብቶች እንደሚተላለፍም ጠቁመዋል፡፡

ከዚህ ቀደም በተለይም በግብርና እና ሌሎም ኢንቨስትመንቶች የተሰማሩ ባለሃብቶች በገቡት ውል መሰረት በሚገባ ስራቸውን እንዲያከናውኑ  ብርቱ ክትትል እንደሚደረግ አመልክተዋል፡፡ 

የኢንቨስትመንት መሬት ወስደው ያላለሙ ባለሃብቶች ያለምንም ቅድመ ሁኔታ መሬት ከመንጠቅ ጀምሮ  እርምጃ እንደሚወሰድ አስታውቀዋል፡፡ 

 

 

  

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም