ቀጥታ፡

በአዲስ አበባ በሁሉም መስኮች የሚከናወኑ የልማት ፕሮጀክቶች የሰውን የኑሮ ሁኔታ በማሻሻል ተጨባጭ ለውጥ እያመጡ ነው - ከንቲባ አዳነች አቤቤ 

አዲስ አበባ ፤ ነሐሴ 29/2015 (ኢዜአ)፡- በመዲናዋ በሁሉም መስኮች የሚከናወኑ የልማት ፕሮጀክቶች የከተማዋን ገጽታ በመቀየር ብቻ ሳይሆን የሰውን የኑሮ ሁኔታ በማሻሻልም ተጨባጭ ለውጥ እያመጡ መሆኑን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ። 

በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅትና በከተማ አስተዳደሩ ትብብር "አዲስ አበባ የኢትዮጵያ ተምሳሌት" በሚል መሪ ሀሳብ የተዘጋጀው 14ኛው "ስለ ኢትዮጵያ" የፓናል ውይይት ዛሬ ተካሂዷል።

በመድረኩ የመነሻ ጽሁፍ ያቀረቡት የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታው ዶክተር እዮብ ተካልኝ በኢትዮጵያ የተለያዩ የልማት ፕሮጀክቶች እየተከናወኑ መሆኑን ገልጸዋል። 

ከእነዚህም መካከል በርካቶቹ በተያዘላቸው የጊዜ ገደብ በፍጥነት እየተጠናቀቁ መሆኑን አመልክተዋል።

የፕሮጀክቶቹ አፈጻጸም ኢትዮጵያ በቀጣዮቹ ዓመታት ልትደርስባቸው በእቅድ የያዘቻቸው ግቦች እውን ሊሆኑ እንደሚችሉ አመላካች መሆናቸውን ጠቁመዋል። 

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ በበኩላቸው በመዲናዋ እየተከናወኑ ያሉ የልማት ፕሮጀክቶች የከተማዋን ገጽታ ብቻ ሳይሆን የሰውን ኑሮ የቀየሩ ናቸው ብለዋል።

ጎን ለጎንም መዲናዋ የሁሉም እንደ መሆኗ መጠን ለምጣኔ ሃብታዊ እድገቷ የሁሉም ዜጋ ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑንም አንስተዋል።   

በመሆኑም ሁሉም ተባብሮና ተጋግዞ ለመዲናዋ ከፍታ ሊሰራ እንደሚገባ ነው ያሳሰቡት።

በተያያዘም የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳድር ጋር በመተባበር ያዘጋጀው 14ኛው "ስለ ኢትዮጵያ" የፎቶ አውደ ርዕይ በከንቲባ አዳነች አቤቤና በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ጌትነት ታደሰ ተመርቆ ዛሬ ለዕይታ ክፍት ሆኗል።

የፎቶ አውደ ርዕዩ በአዲስ አበባ ከተማ በተለያዩ ዓመታት የነበሩ ገጽታዎችን፣ የከተማዋን ልዩ ልዩ ስራዎችን፣ ሜጋ ፕሮጀክቶችን፣ ሰው ተኮር ተግባራትን ጨምሮ ልዩ ልዩ ሁነቶችን የሚያሳዩ ሥራዎች ተካተውበታል።

የፎቶ አውደ ርዕዩ እስከ ጳጉሜን 6 ቀን 2015 ዓ.ም ድረስ ለእይታ ክፍት ሆኖ እንደሚቆይ ተገልጿል።

  

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም