ቀጥታ፡

በአማራ ክልል  ከተሞች  የመሰረተ ልማት ችግሮችን ለመፍታት  ቅድሚያ ሰጥተን እንሰራለን - ዶክተር አህመዲን መሀመድ

ባህር ዳር፤  ነሐሴ 29/2015 (ኢዜአ)፡-  በአማራ ክልል  ከተሞች  የመሰረተ ልማትና ሌሎችንም  ችግሮችን  ለመፍታት ቅድሚያ ሰጥተን እንሰራለን ሲሉ በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የከተማ ልማት ዘርፍ አስተባባሪ ፣ የከተማና መሰረተ ልማት ቢሮ ኃላፊ ዶክተር አህመዲን መሀመድ  ገለጹ።

በቅርቡ  የተሾሙት ዶክተር አህመዲን መሀመድ  ከሚመሯቸው ተቋማት የስራ ኃላፊዎች ጋር የተዋወቁ ሲሆን፤ ቀጣይ የትኩረት አቅጣጫዎችን አመላክተዋል።

በወቅቱ እንደተናገሩት፤ በአዲስ የተደራጀው አመራር የህዝብን አንገብጋቢ ጥያቄዎችን ለመመለስ በመለየት ቅድሚያ ትኩረት ሰጥቶ ይሰራል።
 

በዚህም ከተሞች የገቢ አቅማቸውን አሟጠው በመሰብሰብ በህዝቡ የሚቀርቡ ቅሬታዎችን በፍጥነት ለመፍታት ተባብሮ መስራት እንደሚጠይቅ ገልጸዋል።

በተለይም የከተሞችን ዘላቂ እድገት ለማረጋገጥ የመሬት አያያዝና አጠቃቀም እንዲሁም አስተዳደር ስርዓት በማዘመን ብልሹ አሰራሮችን የማስተካከል ስራ እንደሚከናወን ተናግረዋል።

በተጨማሪም በከተሞች የሚስተዋለውን የመሰረተ ልማት ፣ የአገልግሎት አስጣጥ፣ የመኖሪያ ቤት አቅርቦት እጥረትና የስራ አጥነት ችግሮችን ለመፍታት ቅድሚያ ሰጥተው እንደሚሰሩ ገልጸዋል።

የስራና ስልጠና ተቋማትን በማደራጀት ስልጠና መስጠት፣ የአንድ ማዕከል አገልግሎትን ማስፋፋትና ዘመናዊ የገበያ መረጃ ስርዓት መዘርጋት በትኩረት የሚከናወኑ ተግባራት ናቸው ብለዋል።

በንግድ ዘርፍም የምርት አቅርቦት እጥረት ችግርን ማቃለል የሚያስችሉ የገበያ ማዕከላትን ተደራሽ በማድረግ ህብረተሰቡ በአቅራቢያው ግብይት የሚፈፅምበት ምቹ ሁኔታዎች እንደሚፈጠሩ ተናግረዋል።

ለዚህም እየተስተዋለ ያለውን ፅንፈኝነትና ሌብነትሁሉም አምርሮ  በመታገል በአዲስ አስተሳሰብና እይታ ችግሩን  በማስተካከል የተገኘውን ሰላም አጽንቶ ማስቀጠል እንደሚገባ ተናግረዋል።

ተቋማት ጠንካራ የአሰራር ስርዓት በመዘርጋትና የስራ አፈፃፀሞችን በየጊዜው በጋራ በመገምገም ህዝብን ተጠቃሚ የሚያደርጉ መልካም ውጤቶችን ለማስመዝገብ በጊዜ የለኝም ልንረባረብ ይገባል  ሲሉም አሳስበዋል።

የክልሉ ገቢዎች ቢሮ ኃላፊ አቶ ክብረት መሀመድ በበኩላቸው፤ ክልሉ የሚያመነጨውን ገቢ አሟጦ በመሰብሰብ ለክልሉ ልማትና ዕድገት ለማዋል የዘርፉ ተቋማት በቅንጅት ሊሰሩ እንደሚገባ አመልክተዋል።

በዚህም በበጀት ዓመቱ ለመሰብሰብ የታቀደውን 71 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር ገቢ ለማሳካት የተቋማትን ቅንጅታዊ አሰራር በማጠናከር እቅዱ ግቡን እንዲመታ በትኩረት ይሰራል ብለዋል።
 

የመሬት አስተዳደር ስርዓትን ለማዘመን በገጠር ብዙ ርቀት ተጉዘናል  ያሉት ደግሞ የክልሉ መሬት ቢሮ ኃላፊ አቶ ሲሳይ ዳምጤ ናቸው።

በቀጣይም በከተሞች አሰራርን  በማዘመን ከመሬት ጋር ተያይዞ የሚነሱ ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት  እንደሚሰራ ገልጸዋል። 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም