ቀጥታ፡

በቀጣዩ አንድ ወር የሚኖረው እርጥበት ለግብርና ሥራ አመቺ ሁኔታ ይፈጥራል - የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት

አዲስ አበባ ፤ ነሐሴ 29/2015 (ኢዜአ)፡- በቀጣዩ አንድ ወር ውስጥ የሚኖረው እርጥበት ለግብርና ሥራ አመቺ ሁኔታ እንደሚፈጥር የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት ገለፀ።

ኢንስቲትዩቱ ዛሬ ለኢዜአ በላከው መግለጫ እንደገለጸው በቀጣዩ አንድ ወር የሰሜን ምዕራብ፣ የምዕራብና የመካከለኛው የአገሪቱ ክፍሎች ከመካከለኛ እስከ ከባድ መጠን ያለው ዝናብ እንደሚያገኙ ይጠበቃል ብሏል።

የአየር ሁኔታው በቀጣይ ለሚከናወኑት የግብርና እንቅስቃሴ በተለይም ዘግይተው ለተዘሩና በእድገት ደረጃ ላይ ለሚገኙም ሆነ ፍሬ በመሙላት ላይ ላሉት ሰብሎች ጠቃሚ እንደሆነ ገልጿል። 

የዝናቡ ሁኔታ ለቋሚ ተክሎችም  የውሃ አቅርቦት የሚረዳ ሲሆን በክረምት ወቅት መጨረሻ በደጋማው አካባቢ ለሚዘሩ የጥራጥሬ ሰብሎች አመቺ ሁኔታን እንደሚፈጥርም ጠቁሟል።  

በተጨማሪም ለአርብቶ አደርና ለከፊል አርብቶ አደር አካባቢዎች ለእጽዋት ልምላሜና ለመጠጥ ውሃ አቅርቦት መሻሻልም እንደሚረዳም እንዲሁ።

በተለይም ባለፉት የክረምት ወራት በመደበኛ ሁኔታ ደረቅ ሆነው በሰነበቱና በጋ ሁለተኛ የዝናብ ወቅታቸው ለሆኑት የደቡብ ኦሮሚያና የደቡብ ምስራቅ አካባቢዎች የጎላ አስተዋጽዖ እንደሚያበረክትም አመልክቷል።

በሌላ በኩል ደግሞ ከመደበኛ በላይ ዝናብ በሚጠበቅባቸው በአንዳንድ ቦታዎች እርጥበቱ ከመጠን በላይ  ሊሆን ስለሚችልም በዚህ ምክንያት ማሳ ላይ ውሃ እንዳይተኛ ቦይ ማውጣት እንደሚያስፈልግ ኢንስቲትዩቱ አሳስቧል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም