ኢትዮጵያ በሩጫ ውድድር ያላትን አስደናቂ  የድል ታሪክ በሌሎች የአትሌቲክስ ዘርፎች ለመድገም በትኩረት ሊሰራ ይገባል - የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ቀጄላ መርዳሳ

አዲስ አበባ ፤ ነሐሴ 29/2015 (ኢዜአ)፡- የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን በሩጫ ውድድር የተመዘገቡ አስደናቂ ድሎችን በሌሎች የአትሌቲክስ ዘርፎች ለመድገም በትኩረት መስራት እንዳለበት የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ቀጄላ መርዳሳ ገለጹ።

በሀንጋሪ ቡዳፔስት በተካሄደው 19ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ለተሳተፉ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ትናንት የዕውቅና እና ሽልማት መርሀ ግብር ተካሂዷል።

በመድረኩ ላይ ንግግር ያደረጉት የባህልና ስፖርት ሚኒስትር አቶ  ቀጄላ መርዳሳ፣ በተሰማሩበት ሙያ ታላቅ ገድል እና የላቀ ውጤት ያስመዘገቡ ሰዎችን መሸለምና ዕውቅና መስጠት አስፈላጊ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ 

በአትሌቲከስ ሻምፒዮናው ኢትዮጵያን ከፍ ላደረጉ አትሌቶች የተሰጠው ሽልማት ዓላማውም በቀጣይ የተሻለ ውጤት እንዲያመጡና ለትውልድ አርዓያ እንዲሆኑ ነው ብለዋል።

በቡዳቤስት ለተገኘው ውጤት በውድድሩ የነበረው የቡድን ስራ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከቱን የገለጹት ሚኒስትሩ፣ በቀጣይ ያሉ ክፍቶችን በማረም ለተሻለ ውጤት መሰራት እንደሚገባ ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ በአትሌቲክስ ዘርፍ የረዥም ዘመን የድል አድራጊነት ዕውቅና ያላት ሀገር መሆኗን ገልጸው በሌሎች የውድድር መስኮችም ይህንን መድገም እንደሚያስፈልግ አንስተዋል።

ለዚህም የኢትዮጵያ አትሌቲከስ ፌደሬሽን በቀጣይ ከሩጫ ውድድር ባሻገር በሌሎች የአትሌቲክስ ስፖርታዊ ውድድሮች ላይ በትኩረት መስራት አለበት ነው ያሉት።

የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ረዳት ኮሚሽነር ደራርቱ ቱሉ በበኩሏ፤ በቡዳፔስት በአስቸጋሪ አየር ሁኔታ ውስጥ የተገኘው ውጤት እንደተጠበቀው ባይሆንም ትልቅ ውጤት ነበር ብላለች።

በውድድሩ የታዩ ደካማ ጎኖችን በማረም በቀጣይ በፓሪስ በሚካሄደው የኦሊምፒክ ጨዋታዎች ውድድር ላይ የተሻለ ውጤት ለማምጣት እንደሚሰራ አረጋግጣለች።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም